Eyayu the Fungus: My Plastic Bag-Part 1 ("እያዩ ፈንገስ- ፌስታሌን" ባለ አንድ ሰው የሙሉ ሰዓት ቴአትር-ክፍል ፩)

“One–Man-Show” a New insight in Ethiopian Theater

ቴአትር ቅብብሎሽ ፣ከአንድ ስው መነባንብ ወደ ንግግር እያደገና እየዳበረ የሚሄድ ፣ በተለያየ ዘውጎች ተቀናብሮ እና ማስተላለፍ የፈለገውን መልእክትና እውነት ይዞ የሚቀርብ የኪነጥበብ አውድ ነው፡፡ በተለይ በሀገራችን የቴአትር ታሪክ ውስጥ ከወጥ እሰከ ውርስ ትርጉም ስራ ከአሳዛኝ እስከ አስቂኝ ፤ ከሽሙጥ እስከ ስላቅ ያሉትን ዘውጎች አስተናግዷል፡፡ ከዚህ ባለፈ አስር ሰው ከማይሞሉ እሰከ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎችን ያስተናገዱ የሙሉ ሰዓት ተውኔቶችን ማየትም ችለናል (የሙሉ ሰዓት ተውኔት እስከ ሁለት ሰዓት የሚፈጅ ተውኔት ማለት ነው)፡፡

በ20 ኛው ክፍለ ዘመን የዘመናዊ የኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ መባቻ ላይ እነ በጅሮንድ ተክለሐዋሪያት ተክለማሪያም ሃይማኖትን ከስነምግባር እንዲሁም ፖለቲካን ካለው የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር እያስተያዩ ያለውን ክፍተት ለህዝቡ በማድረስ ሀሁ ማለት የቻሉ የቴአትር አበው ነበሩ፡፡ ማኅበረሰባዊ፣ ቤተሰባዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸውን ተውኔቶችን በመፃፍና በማዘጋጀት ህብረተሰቡን በስነምግባር ለማነጽ ብሎም ግብረገብነትን ለማስረጽ አሌ የማይባል ሚና ተጫውተዋል፡፡ በተለይም በቤተክርስቲያን ትምህርት የተቃኙት ዮፍታሔ ንጉሴ ፣ መላኩ በጎ ሰው እና እዩኤል ዮሐንስ ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ላለፉት ሶስትና አራት አስርት አመታት በተለይም በ1950ዎቹና 60ዎቹ ውስጥ ከሀገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት ጋር አብረው መውጣትና መውረድ ፤ የህዝቡን የልብ ትርታ ማድመጥ የቻሉ ተውኔቶችን መመልከት የተቻለበት አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ እንደ እነ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን እና መንግስቱ ለማ ያሉ ጸሀፍት ቀላል የማይባለውን የኪነጥበብ አብዮት ፈጥረው በመንግስትና በህዝብ መካከል እንደ እግዜር ድልድይ ጽኑ ሆነው አልፈዋል፡፡ በተለይም ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሂሳቸውን በሰላ ብዕራቸው በመንቀስ ቴአትርን ጥሩ መሳሪያ ምናልባትም እምቅ ስሜትን መተንፈሻ አድርገውት አልፈዋል፡፡

በደርግ ስርዓት ኪነጥበብ የነበረውን የሶሻሊዝም ስርዓት ለማድመቂያነት ብሎም የነበረውን የእርስ በርስ ሽኩቻና ጦርነት ምክንያት በማድረግ ለማዝመቺያነት እና ወኔን ለመቀስቀሻ ዋነኛ መሳሪያ አድርጎት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቴአትር በ21ኛው ክፍለዘመን ንግድ ተኮር ይዘት ያላቸው በተለይም የእለት ተዕለት ኑሮአችንን በመዳሰስ ማህበረሰባዊ ክፍተታችንንና ዝቅጠታችንን ለማሳየት የሞከሩ እንደነበር አይዘነጋም፡፡እነ ጌትነት እንየው ፣ ማንያዘዋል እንደሻው ለዚህ ዘመን ባለታሪክ ናቸው፡፡ ይሁንና የስርዓቱ አንድ ጽንፍ ትላንት የነበረውን ማኅበረሰባዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ሂሶችን በአግባቡ ማስተናገድ የዳገት ያህል ከባድ ሆኖበት ነበር፡፡ ኅብረተሰቡ ይዞት ከመጣው ልማድ አንፃር ቴአትር አፍም ጆሮም እንዲሆን የተመልካቹ ፍላጎት ቢሆንም የኪነጥበብ ልሂቃንም ይህንን እውነታ መሰረት አድረገው መጓዝ አልቻሉም ነበር፡፡ ብዙዎቹ ተጀምረው የቆሙ ገሚሶቹ ደግሞ በታሪካዊ ተውኔቶች ተሸፋፍነው የትላንትን ጉልበትና አቅም ለመፍጠር የሚፍጨረጨሩ ነበር፡፡ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ በግልጽ መጋፋጥ የሚያቅትበት ደረጃም እስከሚያደርስ ድረስ ብዚዎችን ለፈተና ያጋለጠበትም ወቅት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህንን አካሄድ ለመግታት እንደ አማራጭ የተወሰደው እርምጃ የሚመስለው የኅብረተሰቡን ስሜት ከአንድ ጽንፍ ወደ ሌላ ጽንፍ ማሻገር … ከሀዘን ተኮር ወደ አስቂኝ የቴአትር ዘውግ መቀየር (the dynamic shift of genre- from Tragedy to Comedy) ፤ የኅብረተሰቡን የፖለቲካ ጥያቄ መልስ ከመስጠት በታሪካዊ ተውኔቶች ማንነቱንና ኢትዮጵያዊነቱን እየነገሩ ማስታገስ ብሎም ግብረገባዊ ሚናን መጫወት ፤ የኪነጥበብ ስልታዊ ማፈግፈግ እስኪመስል ድረስ በዚህ ቅኝት ውስጥ ማለፍ ግድ የሆነ ይመስላል፡፡ ይህ ዛሬ ያለንበትንም እውነታ ያመላክታል፡፡

ቴአትር በርግጥም ራስን መፈተሻ ብሎም ራስን መመልከቻ መስታወት እንደሆነ እሙን ቢሆንም በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ውስጥ በነበረው ስርዓት መታሸቱ ፣ እንደየፖለቲካው ርዕዮት ዓለም መቃኘቱ አልቀረም ነበር፡፡ በዚህ ፍትጊያ ውስጥ ደግሞ የኅብረተሰቡ ጥያቄ ሁሌም መልስ የሚሻ ሆኖ ይታያል፡፡ ኪነጥበብ ዛሬም መሳሪያነቷ እንደ እውነት የፈጠጠ ሀቅ ሆኗል፡፡ ኅብረተሰቡ አፉ ሲሸበብበት የኪነጥበብን አፍ መዋስ ግድ የሚሆንበት ጊዜ ቀን ቆጥሮ ይመጣል፡፡ በተለይ ቴአትር የኅብረተሰቡን የውስጥ ጥያቄ ና ተናፋቂ ሰላም ለማምጣት በስላቅም ይሁን በምጸት ፤ በሳቅም ይሁን በሀዘን ስሜት ፣ እውነታን ባዘለ አቀራረብም ቢሆን ኅብረተሰቡን እንዲመስል ይፈለጋል፡፡ እንደ አኗኗር ይትባህል ጥግ የምንወድ ህዝቦች እንደ መሆናችን መጠን ፊት ለፊት ከመጋፈጥ ይልቅ በአሽሙርና በነቆራ መቆንጠጥ የምንወድ ፣ በሾርኔ የምንሸነቁጥ ጫን ሲልም በቅኔ ወጋ የምናደርግ ብሎም በሟሽሟጠጥ የሳማ ልምጭ የምንለበልብ በመሆናችን ለዚህ ከቴአትር የበለጠ የልብ አድርስ አንጀት አርስ ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡
ክፍል ሁለት ይቀጥላል....

በትዕግስት ካሳ /አዲስ አበባ


Comments (1)

or to write a comment

Dave David

Dec. 8, 2018, 1:10 a.m.

Can't wait to the second part of this.

Latest News and Articles

Ethiopian movie news and article - Asansiro
read more