June 17, 2017, 1:58 p.m. by Tigist
....ከክፍል ፩ የቀጠለያለንበት ወቅት ምንም እንኳ በሀገርኛ ፊልሞች እንደ አሸን መፍላት ምክንያት ቴአትራችን የመዋጥ ዕጣ ፈንታ ቢገጥመውም በተለያየ አጋጣሚ ለማንሰራራት እየሞከረ ይታያል፡፡ ባለ አንድ ሰው የሙሉ ሰዓት ተውኔት ፣ ባለ ሁለት ሰዎች ዘመናዊ ቴአትር በአዲስ አቀራረብና ይዘት የቴአትርን ሌላ ገጽታ ማሳየት ጀምረዋል፡፡ ከተለመደው የቴአትር አቀራረብ ወጣ በማለት ማሳያ ቦታውንም ጭምር በመቀየር ከቴአትር ቤት ወደ ፊልም ቤቶችና ሆቴሎች በማሻገር የተመልካቹን ፍላጎት በሌላ አቅጣጫ የማሟላት አካሄድን ዘይደዋል ማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡
የ21ኛው ክፍለዘመን ማብቂያ አዲስ ዕይታ ለኢትዮጵያ ቴአትር… "እያዩ ፈንገስ- ፌስታሌን" የሙሉ ሰዓት ቴአትር በአንድ ሰው ብቻ ሳያሰለች በአንድ ገቢርና መቼት ተወስኖ በአራት ክፍል ተከፍሎ ሲቀርብ ማየት ፤ ከአስቂኝ እስከ አሳዛኝ ከሽሙጥ እስከ ስላቅ ያሉትን ዘውጎች ያማከለ ፤ በአንድ ሰው ውስጥ ብዙዎችን ማየት ያስቻለ አዲስ የተውኔት ጅማሮ፡፡ በሌላው ዓለም One-Person-Show/One-Man or Woman- Show ተብሎ የሚታወቀው ይህ የቴአትር አቀራረብ በዘመናዊው የኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ውስጥ አሻራ ጥሎ ማለፍ የሚችል ቴአትር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከንግግር ወደ መነባነብ የተለወጠ ምናልባትም ንግግርን በምናብ ከተሳሉ ገጸ ባህሪያት ጋር በማዋሀድ ለማሳየት የተሞከረበት (Solo Performance)ነው፡፡
እንደ ቴአትር መምህሩ ፋንታውን እንግዳ አገላለጽ "One Man Show" "አሀዳዊ ተውኔት" በሚል ፍቺ በአንድ ሰው አብላጫውን የማየት ጥበብ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በርግጥ በአሀዳዊ ተውኔት ውስጥ ተዋናዩ (The Solo Performer) የተለየ የትወና ብቃት ሊኖረው እንደሚገባ የሚጠበቅ ቢሆንም የሚያነሳው ጭብጥ ግን በራሱ ሊያጫውተውና ከተመልካቹ ጋር ሊያገናኘው ብሎም ሊያስተሳስረው ግድ ነው፡፡ በአለምአቀፍ ደረጃ ስለ አሀዳዊ ቴአትር ሲነገር ብዙዎች በተለምዶ ከህዝባቸው ፊት ቆመው ታሪክን የማውራት፣ የመተረክ ፣ንግግር የማድረግ ተለምዷዊ ስርዓት እንደነበር በማውሳት እንደመነሻ አድርገው ይወስዱታል፡፡ በዚህም አጋጣሚ አፈታሪኮች ፣ በወረቀት መስፈር ያልቻሉ ኣባባሎችና አነጋገሮች ለትውልድ የተላለፉበት አጋጣሚም በዚህ እንደነበር ይነገራል፡፡ በቴአትር ታሪክ ዕድገት ውስጥ የሚነሱት የግሪክ አነብናቢዎቻቸው (Monologist) እንዲሁም በመካከለኛው ዘመን የነበሩት የእንግሊዝ ሞዛቂዎችና የፈረንሳይ ሙዚቃን ከግጥም ጋር የሚያቀናብሩ ጥበበኞች አሀዳዊ ተውኔትን እንዳሳደጉት ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ በሀገራችን ግን ሃምሳ ዓመታትን ጠብቆ በመሃል ብቅ ጥልቅ ከሚሉ መነባንባዊ ድራማዎች (realistic monologue dramas) ባለፈ በአንድ ሰው ብቻ የሚተወን ተውኔት "እያዩ ፈንገስ- ፌስታሌን" ሆኗል፡፡ ወደ አስራ ስድስት ያህል ተከታታይ ክፍሎችን በተለያየ መድረክ ያስተናገደው ይሄው ተውኔት አሁን በመሉ ሰዓት ተውኔትነት በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ እንደ ጭብጥ የሚያነሳቸው ሃሳቦች የሰውን ልብ መኮርኮር የሚያስችል ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት በስነምግባር እና በግብረገብ ለማነጽ የሚጥሩ ተውኔቶችን ለመድገም የቻለ ፣ከጎምዛዛ ሂስ ይልቅ በአሽሙርና በሽሙጥ በቅኔና በሾርኔ አኗኗራችንን ከክፍተታችን ማሳየት የቻለም ተውኔት ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በግልጽ ማውራት ያልቻለውን እውነት፣ የመናገር ሰብዓዊ መብቱ እንደተሸረሸረበትና አፉ እንደተሸበበት ማሳያ ከመሆንም ባለፈ ዛሬም ኪነጥበብ ድምጼ ናት ብሎ በልቡ መፈክር እንዲያሰማ እድል የፈጠረ ቴአትር ነው፡፡ ሂስ፣ ነቆራ ፣ ሽንቆጣ በሳቅም በለቅሶም ታጅቦ ሲቀርብ ማንነታችንን ፣ ሰብዓዊነታችንንና ሰዋዊነታችንን፣ ፖለቲካችንን ማኅበራዊ መስተጋብራችንን በአጠቃላይ እንደ ሀገር እንደ ህዝብ ወዴት እየተጓዝን ነው ለሚለው ማሳያ የተውኔት መስታወት ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ እዚህ ጋር አንድ መሰረታዊ ነጥብ ማንሳት ግድ ይላል፡፡ እንደ አሃዳዊ ተውኔት በአንድ ሰው ውስጥ በርካታ ገጸ ባህሪያትን በማካተት ከንግግር ወይም ምልልስ (dialogue) የጸዳ ለማድረግ ፈታኝ እንደሆነ ለማየት ይቻላል (Monologue or Dialogue?)… አንድ ሰው ውስጥ አስር ሰዎቹ አሉ እንደማለት…
ከዚህ ውጪ ግን እንደ ትዝብት ዛሬም ጥግ ፈላጊና ሸሺዎች ፤ ፊት ለፊት ተጋፋጭና ተፋላሚዎች አለመሆናችንን "እያዩ ፈንገስ- ፌስታሌን" የሙሉ ሰዓት ቴአትር ውስጥ እናየዋለን፡፡ እያዩ መምህር የነበረ በሰዎች ክፋትና ሰዋዊ ባህሪይ መጓደል (እሱ ፈንገሳችን በሚለው ሰዋዊ ድክመታችን) በወሊድ ምክንያት የሚወዳት ባለቤቱን ያጣ በህመም ምክንያት ደግሞ ልጁንም በሞት የተነጠቀ ፤ በዚህ ሀዘንና ጭንቀት ውስጥ ለአዕምሮ ህመም የተጋለጠ በእኛ ነባራዊ አገላለጽ "እብድ" የምንለው ዓይነት ሰው ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የቴአትሩ ጭብጦች በሌላ ማንነት ቢገለጹ ኖሮስ የሚል ጥያቄ ማጫሩ ግድ ይመስላል፡፡ "እብድና ዘመናይ የልቡን ይናገራል" ብለን መሸሸጊያ ካልፈጠርን በቀር፡፡ የፈሪ በትር ዓይነት መከለያችን ፣ እውነትና ልክ ልክ ነጋሪያችን ፣ ተንባያችን -ነጋችንን ነጋሪ ፣ አሽሟጣጪያችን እብድ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር መስጋት ያስፈልጋል.. ሁሉም በልቡ የሚያጉተመትመው እውነታ ነውና፡፡
በመጨረሻ ማንሳት የሚያስፈልገው እውነት ቴአትሩ በሁለት ዓይነት ተመልካች የተከፈለ መሆኑን ነው… ሽሙጥ ፣ አሽሙርና ስላቅ የማይገባው ተመልካች እና በቅኔያዊ አነጋገር የበለጸገ ተመልካች፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ሾርኔ አይዘልቀውም ፣ በሽሙጥ ነገር አይፈትልም ፣ ቅኔን በሰምና ወርቅ መፍታት አልመደም….እናም ነገር ሁሉ ዘግይቶት ነው የሚገባው፡፡ የአማርኛው ጥልቀት ብዙዎችን ለመረዳት እንዳንገዳገዳቸው እሙን ነው፡፡ ሳቁ እያሸነፈ ክፍተቱን መሙላት ቻለ እንጂ ቴአትሩን ለማየት ከሚገባው ደርዘን ሙሉ ተመልካች ምን ያህሉ ገብቶታል ምንያህሉስ ሳቁን ብቻ ጨርሶ ወጥቷል ለመገመት ይከብዳል፡፡ ሲጠቃለል "እያዩ ፈንገስ- ፌስታሌን" የሙሉ ሰዓት ቴአትር በአንድ ሰው ብቻ ሳያሰለች በአዲስ አቀራረብ የመጣ በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ውስጥ አሻራ ጥሎ የሚያልፍ የቴአትር ዘውግ መሆኑን መመስከር ግድ ይላል፡፡ ደራሲው በረከት በላይነህ እንዲሁም ተዋናዩ ግሩም ዘነበም የዚሁ ታሪክ ተቋዳሽና ባለታሪክ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡
ሰኔ 2009በትዕግስት ካሳ /አዲስ አበባ