79. The Movie! (መሥራት ጀግንነት ነው፤ ማድነቅ መሰልጠን ነው!)

ይህ ተካበ ታዲዎስ ፤ (ይህ የጥበብ ገበሬ) ‹79 - ሠባ ዘጠኝ› ፊልም ይዞ እየመጣ ነው ተካበ ታዲዎስ ይባላል፡፡ ልጅ እያለ ለሚያያቸው ፊልሞች ከፍተኛ ፍቅር ነበረው፡፡ ለእናቱ ፈለቀች ጌታሁን የልጅነት ሕልሙን ይነግራት ነበር፡፡ ‹‹እቴቴ … ትልቅ ስሆን ፊልም ሰሪ እሆናለሁ›› ይላታል፡፡ እናቱም ‹‹እንዳፍ ይሁንልህ ልጄ!›› ብሏው መርቀዋለች፡፡ የእናቱ ምርቃት እዚህ ደርሷል … የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን እንዳለፈ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመደበና የኢኮኖሚክስ ትምህርቱን መከታተል ጀመረ፡፡ በ1999 እና በ2000 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ በትርፍ ጊዜው ፊልም ኤዲቲንግ እና ካሜራ ቀረጻ እየተለማመደ ሁለት የተማሪ ፊልሞችን ሰራ፡፡

ትምህርቱን እንደጨረሰ በትምህርት ሚኒስቴር በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ሆኖ ተቀጠረ፡፡ ነገር ግን ከሚወደው የፊልም ሥራ መለየት ስላልቻለ ከአንድ ዓመት አስተማሪነት በኋላ ሥራውን ትቶ በናዝሬት፤ (አዳማ) ከተማ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን ፊልም ለመስራት እንቅስቃሴ ጀመረ፡፡ ተካበ - በ2004 ዓ.ም. ‹ዳይናማይት› የተሰኘ ፊልሙን ሰርቶ ለተመልካች በማቅረብ ከፍተኛ ተቀባይነትን አገኘ፡፡ ይህ ፊልም በጣም በዝቅተኛ በጀት የተሰራ ቢሆንም በተመልካች ዘንድ ተወዳጅነትን አግኝቶ በመጀመሪያው የጉማ ፊልም ሽልማት በብዙ ዘርፍ በመታጨት ለመሸለም በቅቷል፡፡ ኋላም ከገንዘብ እጥረት የተነሳ ናዝሬት የነበረው ቡድን ሲበተን ተካበ በአዲስ አበባ ካም ግሎባል ፒክቸርስ መሥራት ጀመረ፡፡ በ2005 ዓ.ም. በተሰሩት ‹ወደ ገደለው› እና ‹አማረኝ› ፊልሞች ላይ የኤዲቲንግ እና ቪዥዋል ኢፌክትስ ሥራዎችን የሰራ ሲሆን ቀጥሎም ‹400 ፍቅር›፣‹ረቡኒ›፣‹ዘውድ እና ጎፈር›፣‹ከእለታት› እና ‹መባ› ፊልሞች በግራፊክስ እና በኤዲቲንግ የሰራባችው ፊልሞች ናቸው፡፡

ይህ ተካበ ታዲዎስ ፤ (ይህ የጥበብ ገበሬ) በ2006 ዓ.ም. የቀድሞ የስራ ጓደኞቹን በማሰባሰብ አንድ ትልቅ የፊልም ፕሮጀክት ጀመረ፡፡ ይህን ሥራ ሲጀምር ብዙዎች ‹‹አትችለውም!›› ፤ ‹‹የኛ ሀገር ቴክኖሎጂ እና ባለሙያ አይሰራውም!›› በማለት ሥራው ላይ መሳተፍ አልፈለጉም ነበር፡፡ ነገር ግን የተካበን ሀሳብ የተረዳው ወጣቱ ስለሺ ጌታነህ እኔ ወጪውን እሸፍናለሁ ብሎ ፊልሙን ፕሮዲዩስ ለማድረግ ተስማማ፡፡ኋላም የ‹79 - ሠባ ዘጠኝ› ፊልም ሥራ ተጀመረ፡፡ በዚህ ፊልም ላይ ግሩም ኤርሚያስ፣ ሠላም ተስፋዬ፣ ናታይ ጌታቸው፣ እንቁስላሴ ወ/አገኘሁ እና ሌሎች ተዋንያን የተሳተፉበት ሲሆን ለሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ አዲስ ነገር ይዞ የመጣ ነው፡፡ ፊልሙ በ1979 ዓ.ም. የነበሩ የሁለት ወጣቶች የፍቅር ታሪክ ሲሆን በወቅቱ በነበረው የፖለቲካና የጦርነት ሁኔታ የሚደርስባቸውን ችግር የሚያሳይ ነው፡፡ በፊልሙ ታሪክ ላይ የተገለፁትን ቦታዎች፣ ቁሳቁሶች እንዲሁም እንደ ጦርነት ያሉ ክስተቶችን ለማሳየት ከቦታ ዝግጅት ጀምሮ በኮምፒውተር ቪዥዋል ኢፌክትስ በመታገዝ አስገራሚ ሥራ ሰርተው አቅርበዋል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጲያ በፊልሙ ዘርፍ በጣም አቅም ያላቸው ወጣቶች አሏት፡፡ ነገር ግን እድሉን ስላላገኙ ወደ ሌላ የሥራ ዘርፍ ይሰማራሉ፡፡ ስለዚህ የተለየ ሥራ ልናይ አልቻልንም፡፡ ይህ ፊልም ግን የነዚህን ወጣቶች ሥራ የሚያሳይ እና ለሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡

‹79 - ሠባ ዘጠኝ› ፊልም በታሪክ፣ በዝግጅት፣ በቅንብር እንዲሁም በልዩ ትወና ቀርቦ ለእይታ ሊበቃ ነው፡፡
ተካበ ታዲዎስ ጽፎ አዘጋጅቶታል፡፡ ስለሺ ጌታነህ ደግሞ ፕሮዲዩስ አድርጎታል፡፡
ሊንኩን ተጭነው የፊልሙን ማስታወቂያ ይመልከቱ፡
• መሥራት ጀግንነት ነው፤ ማድነቅ መሰልጠን ነው!
Like, Comment, Share.Lot's of thanks.

Source Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)፡


Comments

or to write a comment

Latest News and Articles

Ethiopian movie news and article - Asansiro
read more