90 kg vs 40 kg (90 ኪሎ Vs 40 ኪሎ)

'አቅመ-ቢስ' ምን ምን ይበዛበታል እንዲሉ ወይም ጣፋጭ ወሬ ሁሉ አሉታዊ ነገር ብቻ መርጦ ማውራት ይመስል ብዙ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ አማርኛ ፊልሞች 'ደካማ' ጎን በሚመለከተውም በማይመለከተውም ሰው/አካል 'ማውራት' እየተዘወተረ መጥቷል።ለነገሩ ይሄ የትችት ልማድ(ምን ያህል አመክንዮአዊ ነው አይደለም? የሚለው ሌላ ጥያቄ ቢሆንም...እንደኔ ብዙዎቹ ምክንያታዊ ሳይሆኑ ስሜታዊ ሃሳቦች ናቸው።) ብቻ ይሄ የ'መሄስ' ልማድ በኪነ-ጥበቡም ብቻ ሳይሆን በፖለቲካውም በማህበራዊም ይሁን በሃይማኖታዊ(በሌላ አነጋገርም ከሰፈራዊ እስከ አለማቀፋዊ) ርዕሰጉዳይ ላይ እየተዘወተረ መምጣቱን ለማወቅ ፌስቡክ ምስክር መሆን ይችላል።...ለምሳሌ አንድ ፖለቲካዊም ይሁን ሃይማኖታዊ ዜና ከተሰማ "ዝም ማለት እሚያስቀጣ ወንጀል ነው" የሚል አዋጅ የወጣ እስኪመስል ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑቱም የራቁቱም ስለርዕሰ ጉዳዩ አንዳች አስተያየት በተለይ አሉታዊ ነገር ሲያነሱ ታስተውላላችሁ።(የአንዳንዶች አስፀያፊና ወጥ እረግጭ አስተያየት ሳይረሳ)....
አሁን አሁን ምንም ነገር ላይ ለመተቸት የማወራበት አፍ ወይም የምፅፍበት እጅ ካለኝ ብቁ ነኝ ይመስላል መስፈርቱ።....እና እድሉን ካገኘ ማንም ያወራል።ከየትኛውም 'ፊልድ' ቅርብ ስለሆኑንም መሰለኝ በተለይ የኪነጥበብ ውጤቶችን በተለይ ደግሞ የፊልም ስራን መተቸት ለማንም ቅርብ ሆኗል።
(ለነገሩ ስለፊልም የሚወሩ ሃሳቦችን በሙሉ የተመልካች ግብረ ምላሽ በሚል በጥቅል ከመመደብ ውጭ ሂስ ናቸው ብሎ መቀበል ይከብዳል።...ምክንያቱም ሂስ እራሱን የቻለ ስነ ምግባርና ሳይንሳዊ ተግባር ያለው የሙያ መስክ ነውና።)
እና አማርኛ ፊልሞች ላይ ስለሚሰነዘሩ አሉታዊ 'ትችቶች' እንቀጥል።
..ስለ ኢትዮጵያ ፊልም የማያወራ የለም።
አንድ ወዳጄ እንዳለው በኢትዮጵያ ፊልም ላይ ስለጤና በሚያወራ ፕሮግራም ላይ ሁላ አሉታዊ ትችት ሲሰነዘር ታደምጣላችሁ።ስለትራፊክ በሚያወራ ርዕስ ላይ "ፊልሞቻችን ገና አልበሰሉም" የሚል አያገባዊ አሰተያየት ሲሰነዘር ልታደምጡ ትችላላችሁ።ስለ ኢትዮጵያ ፊልም ለማውራት ኢትዮጵያዊ ብቻ መሆን ይበቃ ይመስል ሁሉም ሰው እንደ ልቡ ሲያወራ ታስተውላላችሁ።
ጋዜጠኛው ሙያተኞችንና ሙያው ላይ እየተሳለቀ አሉባልታ ለቃቃሚ ደምበኛ ሊያፈራ ሲማስን ታያላችሁ።ስለኢትዮጵያ ፊልም ሙያተኛውም ያልሆነውም ብቻ ማንም በድፍረት ኢትዮጵያ ውስጥ ፊልም አለ እንዴ?ሊላችሁ ይችላል።እሱ ብቻ አይደለም ወደ ሙያው ለመቀላቀል የሚመጡ ጀማሪ ሙያተኞች አልያ ሙያው ውስጥ እየሰራ ያለ አንጋፋ 'ሙያተኛ'ም በድፍረት ኢትዮጵያ ውስጥ ፊልም የለም! ሲሉ ማድመጥ ብርቅ አይደለም።
ጥያቄው ስለኢትዮጵያ ፊልም አይወራ ሊሄስም አይገባም አይደለም።ሊባልም አይልቻም።በየትኛውም መስክ "ሂስ" ያስፈልጋል።ከግላዊ ሂስ ጀምሮ
በፖለቲካውም በሃይማኖቱም በማህበራዊም ይሁን በሌሎች ጉዳዮችም...በሳል የሂስ ባህል መዳበር ለአንድ ሃገር እድገት የራሱ የሆነ አዎንታዊ ሚና እንዳለው አያጠያይቅም። በጥቅሉ ህይወትን ያለ ሂስ ማሰብ ወጥን ያለጨው እንደማሰብ ነው።እንደ አለመታደል ሆኖ ወይ በሌላ ምክንያት እንጃ ኢትዮጵያውያን በብዙ ፊልድ ብዙ ሃያሲ የለንም።...ወደ ዋናው ሃሳቤ ስመለስ በዚህ ዘርፍ /በፊልሙ ማለቴ ነው/ የሚሰነዘሩ ትችቶች በብዛት መኮራኮም ይበዛባቸዋል።በአስተያየት ብቻ ፊልዱን የሚለቅ እውተኛ ሙያተኛ የለም እንጂ የአንዳንዱ ሰው አስተያየት አስደንጋጭም ነው።
ፊልሞች ላይ ያሰብነውን ሃሳብ ሁሉ ከመጫናችን፤'ወደፊት' የሆነ አስተያየታችንን ከማውራታችን በፊት ወደ ኋላ ትንሽም ቢሆን መንደርደር ያስፈልጋል።
ጎበዝ ፊልም ለመስራት የሙያው ሰው መሆን፣እውቀት(ልምድ)፣ገንዘብ፣ቴክኖሎጂ፣ድጋፍ ሰጪ አሰራር ወይም ምቹ(አበረታታች) የአሰራር ሲስተም (ይሄም ሲባል ከመንግስት የሚመለከተው አካልም ይሁን ከግል የሲኒማ ቤቶች በኩል) እንዲሁም ሌሎች በርካታ ነገሮች ያስፈልጉታል።እድገቱም ከነዚህ ጋር ተሳስሮ የሚመጣ ነው።ፊልም ስራ በፊልም ሰሪዎች ብቻ የሚሰራ ሙያ አይደለም።የመንግስትም የግለሰቦችም የሌሎችም አካላት እገዛ ወይም ድጋፍ የሚፈልግ ነው።የየትኛውም በፊልም ያደጉ ሃገራት ምስጢር/ጀርባ ቢጠና ከዚህ የራቀ ታሪክ የላቸውም።የፊልም ጥበብን ደራስያን፣ አዘጋጆች ፣ተዋንያን፣ሲኒማቶግራፈር፣ኤዲተርና ሌሎች ከካሜራ ጀርባ ያሉ ሙያተኞች ብቻ አያሳድጉትም።...ለፊልም እድገት እኔ አንተ አንቺ እነሱ እኛ ፊልም የማንሰራ ተመልካቾች እንኳ አስተዋፆ አለን።እስኪ የሙያተኞቹን ሚና ለጊዜው እንተወውና(የሚወቀስ ነገር የላቸውም አይደለም።በሚቀጥለው ፅሁፌ በዘርፉ የሚታዩ የሙያውንና የሙያተኞችን ክፍተቶችን ለማሳየት እሞክራለሁ) ብቻ ምን አበረታታች ሁኔታዎች አሉ??
እጠይቃለሁ....መንግስት ለዚህ ሙያ ማደግ ያደረገው ጉልህና ተጠቃሽ ስራ ምንድነው?ትምህርት ቤት ከፍቷል?...ካሜራና መሰል እቃዎች ሲገቡ ቀረጡ ያበረታታል?ፊልም ገምጋሚዎችስ ምን ያህል የቦታው ሰዎች ናቸው?ከፊልም ሰሪው የሚቀበለው ግብርስ ምን ያህል አበረታታች ነው?የግል ሲኒማ ቤቶች አሰራራቸው ምን ያህል ንፁህና እውቀታዊ ነው?..ምን ያህል የግል የፊልም ትምህርት ተቋማት አሉን?መንግስትስ ምን ያህል ይደግፋቸዋል?...ካሉቱስ ምን ያህሉ 'ጥራት' ያለው ትምህርት ይሰጣሉ?የሚዲያ ሰዎችስ ለሙያው ማደግ ምን ያህል እየሰሩ ነው?....ሌሎች ለፊልም ታሪክና እድገት ተግዳሮት የሆኑ ነጥቦችንም ማንሳት ይቻላል?
ስለፊልም ትችት መሰንዘር (ምንም እንኳ ፊልም ሰሪዎቻችን ኩንታል ያህል የሚወቀስ ነገር ያላቸው ቢሆንም)በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሆነው ለሚሰሩ ሙያተኞች እውቅናና ክብር ከመስጠት ሊጀምር ይገባል።ከብዙ ልፋት ጥረትና ብርታት በኋላ ያመጡትን የአሁን ድል ብቻ አይቶ(የኋላ ታሪካቸው ሳይጠና) እነ እገሌ ሃገራት እዚያ ደረጃ ደርሰዋል እኛ ግን ገና እዚህ ነን የሚለው ብያኔም በደምብ ሊጤን ይገባዋል።.....አልያ የሚወራበት ሜዳና 'ተመልካች' ተገኝቷል ብቻ ተብሎ ዳር ሆኖ 'ኢትዮጵያ ውስጥ ፊልም ሰሪም ፊልምም የለም' ብሎ ሾላ በድፍን በሆነ ምልከታ ማውራት ለፊልም ሰሪውም ለመንግስትም ለተመልካቹም ጥቅምም ጥቆማም አይሰጥም።

ኤልያስ ማዳ
መጋቢት 2008


Comments

or to write a comment

Latest News and Articles

Ethiopian movie news and article - Asansiro
read more