Sept. 8, 2018, 11:40 p.m. by EtMDB
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 28፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) "በአዲስ ዓመት ለእናት ሀገሬ" በሚል መሪ ቃል የስጦታ ፕሮግራም በሚሊኒየም አዳራሽ በተከናወነ ስነ ስርዓት በይፋ ተጀምሯል።
ስጦታው በአዲስ አበባ ከተማ በተለያየ ምክንያት በችግር ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች የሚውልና ሁሉም የሚሳተፍበት የአዲስ አመት ስጦታ ሲሆን፥ ከነሀሴ 28 እስከ ጷጉሜን 1 ድረስ የሚቆይ መሆኑም ነው የተገለጸው።
ፕሮግራሙን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀ መኮንን ዛሬ ከሰዓት በኋላ በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን፥ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ባለ ስልጣናትም ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኢዲስ ዓመት ስጦታ ለእናት አገሬ ስጦታ አበርክተዋል።
<>የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው “የዓዲስ አመት ስጦታ ለእናት ሀገሬ” የመስጠትና የማካፈል ልዩ ፕሮግራም ላይ የትምህርት ቁሳቁሶችንና አልባሳት በስጦታ ማበርከታቸውም ነው የተገለጸው።የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች በሚሊኒየም አዳራሽ አልባሳት፣ የተማሪዎች ቁሳቁስ፣ ጫማዎች፣ የታሸጉ ምግቦችና መጠጦች፣ ጥሬ ገንዘብና የደም ልገሳ ሲያደርጉ ውለዋል።ከአዲስ አበባ ከተማ አስሩም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶች የማስተባበር ስራውን እያከናዎኑ እንደሚገኙም ታውቋል።ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የበጎ ፈቃድ ለጋሾች እንደተናገሩት፥ ከቤተሰቦቻቸው ያሳባሰቧቸውን አልባሳት ለዚሁ ጉዳይ ለተቋቋመው ኮሚቴ አስረክበዋል።

ስጦታዎቹ በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች ሊደረሱ እንደሚገባም የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
ደም ምትክ የማይገኝለት ስጦታ ሲሆን፥ በደም እጦት የሚቸገሩ ዜጎችን መርዳት ከዜጎች የሚጠበቅ ሲሆን፥ ሌሎችም በዚሁ ተግባር እንዲሳተፉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።ልገሳው በጥሬ ገንዘብም የሚከናወን ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በአዳረሹ ውስጥ እየተሰበሰበ ነው ተብሏል።
ባለፉት ሳምንታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ወጣቶችና አርቲስቶች የተሳተፉበት በአዲስ ከተማ የአረጋአዊያን ቤት የማደስ፣ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ የማበርከት ስራዎች ሲከናዎኑ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።
Source: FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)