……

Bezawit Mesfin ( ……ሣቅና ደስታዋን ያልነጠቃት ጠንካራና ጉደኛ ፍጥረት)

"ተደራራቢ ፈተና……ሣቅና ደስታዋን ያልነጠቃት ጠንካራና ጉደኛ ፍጥረት!!"
……ቤዛዊት መስፍን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክህሎታቸውን አደባባይ አውጥተው ታዋቂነትን ካገኙ የዘመኑ እንስት ተዋናይት የምትመደብ ናት። ዳና በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ላይ፦ጦሽ የሚያደርጋትና የምትንቀዥቀዥ ነፃ ሴት የሆነችውን የሊያ-ገፀባህሪን ወክላ ባሳየችው ድንቅ የትወና ብቃቷ በሰፊው የታወቀች ሲሆን፤ በሼፉ ቁጥር ሁለት ፊልም ላይ የጨርቆስ ልጅ ሆና የሰራችው ፊልምም ብቃቷን ያሳየችበት ነው!!……ከዚያ ውጪ በተለያዩ ፊልሞች ላይ የተወነችውና ወደፊት ብዙ ተስፋ የሚጣልበት ቤዛዊት ከሙያዋ ውጪ የምትታወቅበት ባህሪዋ ሳቂታነቷ እና በትንሽ ነገር የምትደሰትበት ባህሪዋ ነው።
ከቤዛ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅነው ከአምስት አመት በፊት በታናሽ እህቷ የወንድ ጓደኛ አማካኝነት ሲሆን በወቅቱ፦" የሸረሪት-ድር" የሚለው ፊልሟን ልናሳይ ከሸገር ወጣ ብለን ነበር። ከፍተኛ የፊልም ሽቀላ አለበት ተብለን የሄድነው አምቦ ሲሆን ለሥራ ማከናወኛ እና ለተለያዩ ወጪዎች ብላ ዳጎስ ያለ በጀት መድባልን እኔ እህቷና የእህቷ ፍቅረኛ ቅዳሜ ቀን አምቦ ገብተን ኢትዮጵያ ሆቴል አረፍን።
……ፊልሙ በነጋታው እሁድ ቀን ስለሚታይ በከተማው አለ የተባለ የቁቤ-ቋንቋ ተናጋሪ አስተዋዋቂ ቀጥረን ቀኑን ሙሉ የቅሥቀሣ ሥራ ስንሰራና ፖስተሮች ስንሰቅል ዋልን።
በማግስቱ ፊልሙ የሚታይበት ሰዓት ሲደርስ የተነገረንና የሆነው ግን ፍፁም አይገናኝም!!……በአዳራሹ ወፍ የለም። አምቦ ከተማ ፊልም ሲመጣ ወረፋው ዙሪያ ጥምጥም ሆኖ የሊማሊሞ መንገድ ይመስላል ብሎ በተስፋ የሞላን ልጅ የስራውን ይስጠውና፦ፊልሙ ሊታይ ሲል በአዳራሹ ከፊትና ከኋላ የተገኙት ጥንድ ፍቅረኞች ከርቀት ሲታዩ፦"የላም-ጡት" ይመስላሉ።
በመጨረሻው ሰአት ከአዲስ አበባ የገባችው ቤዛ፦ያ ሁሉ ወጪ አውጥታ እንደነጋዴ ኮረንቲ ትጨብጣለች ብዬ ነበር!!
ባየችው ነገር ፍልቅልቅ ሣቋን ለቃው፦"ምነው ዛሬ አምቦ አፈሳ አለ እንዴ?" አለች። ልፋታችን ገብቷታል፤ እኔ ሺዎች ብር ለወደመባት ሰው ስሳቀቅ እሷ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ሆና እኛን ካፅናናች በኋላ፦" በቃ ለተገኙት አራት ሰዎች ፊልሙን እናሳይ ብለን ከአዳራሹ ሁለት የጥበቃ ሰራተኞች ጋር አንድ ላይ አስር ሆነን ፊልሙን አይተን ጨረስን።
ሲያልቅ፦" ቢዝነስ ሁለት እድል የሚሞከርበት መስክ ነው፤ ወይ ማግኘት ወይ ማጣት!……እጃችንን ወደ ባህሩ ሰደን አሣ ለማግኘት ሞከርን ነገር ግን አሣው አልተገኘም ስለዚህ እጃችንን ከውሃው አውጥተን ከማራገፍ በቀር ከእኛነታችን የሚወስደው ነገር አለ!? ስለዚህ አምቦን ፏ ብለንባት ጠዋት ወደ ሀገራችን!" አለችን።
ምሽቱን ምርጥ እራት ጋብዛን እና እስከክለብ ድረስ አዝናንታን ከሜዳው ውጪ ነጥብ የጣለ ቡድን ሣይሆን ሻምፒዮን አርጋን መለሰችን። በሆኑ ነገሮች ፀጉር የማትነጭ እና መሬት የማትደበድብ ልጅ ናት………ቤዛ!!
ትራጄዲ ሕይወቷ ከልጅነቷ ይጀምራል!……እናትና አባቷን ሞት የነጠቃት ገና በጨቅላነትና ነገሮችን በማታስተውልበት ዕድሜዋ ነው። ዕድገቷ በአያቷ እጅ ቢሆንም እናትና አባትን አጥቶ መኖር ምን ያህል የህይወት ጉድለት እንዳለው ታውቁታላችሁ። ቤዛ የወላጅ ፍቅርና እንክብካቤን ሳታጣጥም ያደገች ልጅ እንደመሆኗ የህይወት ፈተናዋ ከማለዳ ይጀምራል!!……ነገር ግን ራሷን ጠብቃ በምትወደው ሙያ ስኬታማ ብትሆንም በዚህ አጭር ዕድሜዋ መከራ ተፈራርቆባታል። አምቦ የሄድነው ታናሽ እህቷ ነዋሪነቷ አሜሪካን ሀገር የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ ከመጣች ወዲህ የነበረባት የልብ በሽታ ኬዝ ከባድ ስለነበር፦ቤዛ እህቷን ለረጅም ጊዜ ስትንከባከባት ኖራለች፤ ከጓደኛዬ ጋር በፍቅር ተጣምራ የምትኖረው ታናሽ እህቷ በመሀል እርጉዝ ስለነበረች ዶክተሮች ከልብ ችግር ጋር እርግዝና መልካም ያለመሆኑን ሙያዊ ስጋታቸውን ተናግረው ህይወቷ ጭምር በወሊድ ወቅት ሊያልፍ እንደሚችል ቢተነብዩም እግዚሃብሔር እንደሰው አይደለምና የሚያምር ወንድ ልጅ በሰላም ተገላገለች። እንደምንም ፀጥተኛው ገዳይ ከሆነው የልብ ህመሟ ጋር ትታገል የነበረችው ታናሽ-እህቷ በአምላክ መልካም ፈቃድ አንደኛ አመት የልደት በዓሉን በድምቀት ካከበረችለት በኋላ አደራውን ለቤዛ ትታ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች። የቤዛ ሀዘን መራር ነበር!!……አልቅሳ ከወጣላት በኋላ ቀጣይዋ የቤት-ሥራ የአደራ ልጁን እንደእናት የማሳደግ ሀላፊነት ነበርና ይሄው በእቅፏ ያለውን ልጅ ምንም ሳታጓድል እያሳደገችው ትገኛለች።
መቼም በማለዳ መከራ የጀመራት ቤዛዊት ከአመት በፊት ከቼክ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ለስድስት ወር ማረፊያዋ ወህኒ ቤት ከሆነ በኃላ ያን ፈተናም በድል ተወጥታ ኑሮዋን በአዲስ ጀመረች!! ውልግድግድ ያሉ ነገሮችን አስተካክላ ሰላማዊ ህይወትን ቀጠለች። በዚክ አመት መግቢያ ላይ በልጅነት ጉልበቷ ሮጣ የገዛቻትን መኪናዋን እያሽከረከረች 18 ማዞሪያ ከሚባለው ሥፍራ ቁልቁል ወደ ጦር-ኃይሎች መንገድ እያሽከረከረች ነው!!……ቦታው ብዙ የትራፊክ አደጋ የሚከሰትበትና ደም የጠማው መንገድ ነው ማለት ይቻላል። ቤዛ እጇን በመስታወት አውጥታ ወደጉዳይዋ እያመራች ሣለ ፍሬን ለመያዝ ስትል እንዴት እሺ ይበላት!? ደጋግማ ሞከረችው……እግሮቿን እየተጫነች ብትለው እምቢ አለ! ዝም ብሎ የሚፈረጥጠው መኪናዋ ግቡ የት እንደሆነ ሳታውቅ በደመነብስ በመሪ ብቻ እየተጠቀመች ከነፈች!!……ከሞት ጋር ፊት ለፊት ተፋጣለች! ከራሷ ይልቅ የአደራ ልጇን እያሰበች ፀሎትዋን ተያያዘችው! በመጨረሻ በሚበርበት ፍጥነት ከአንድ ግዑዝ ነገር ጋር ተላትሞ ብትንትኑ ወጣ! በሩ ተገንጥሎ እሷ የነበረችበት መቀመጫ ወንበር ለብቻው ተለይቶ ሴፍቲ-ቤልቱ እንቅ እንዳረጋት አሽቀንጥሮ ወረወራት! የእግዚሃብሔር ተዓምር ሆኖ ሰዎች ለእርዳታ ሲደርሱ ቤዛ የፀጉር ቤት ወንበር ላይ የተቀመጠች ያህል አይኗ ይቁለጨለጫል። የሆነው ቅፅበታዊ ክስተት ከፈጠረባት ድንጋጤ በቀር በሰውነቷ ላይ የደረሰ ጭረት እንኳን አልነበረም!!……ጭርምትምት ካለውና ከጥቅም ውጪ ከሆነው መኪና ውስጥ ሰው በህይወት ተረፈ! የተባለ ሰሚ፦"እግዚኦ የአንተ ሥራ!' ከማለት ውጪ ምንም የሚለው ነገር አልነበረም። እኔም ወሬ ለቀማ ሄጄ መኪናውን አይቼ፦" ከዚህ ውስጥ የformula one" የመኪና ተወዳዳሪ እንኳን አይተርፍም ብዬ ተገርሜያለው።
ከቀናቶች በኋላ፦" እግዚሃብሔር እንኳን አተረፈሽ!" ልላት ሄጄ ነበር። ልጅት እንኳን ከአስከፊ የመኪና አደጋ ያመለጠች ይቅርና ከአልጋ ላይ የወደቀች አትመስልም። ስለሁኔታው ስጠይቃት፦" ይሄውልህ ተሜ ሰማይ ቤት ሄጄ በስመ-ሞክሼ ነው ወረፋሽ ገና ነው ብለው መለሱኝ!" አለችና የቤትሆቨን ዜማ የመሰለ ፍልቅልቅ ሣቋን ለቀቀችው! የአደራ ልጇን እየሳመች ምንም እንዳልተፈጠረ ህይወትን ቀጠለች።
"ተደራራቢ ፈተና……ሣቅና ደስታዋን ያልነጠቃት ጠንካራና ጉደኛ ፍጥረት!!" አልኩ በልቤ።
ተመስገን ባዲሶ


Comments (2)

or to write a comment

Dec. 8, 2018, 1:20 a.m.

Beza is awesome!

Dave Face David

Dec. 8, 2018, 1:20 a.m.

Beza is awesome!

Latest News and Articles

Ethiopian movie news and article - Asansiro
read more