Yegir Esat Drama (የእግር እሳት: እሳት ሀሳቦች)

አንድ ውብ የቴሌቭዥን ተከታታይ ድራማ ወደናል፡፡ ወደን ደግሞ ፍቅራችን ከቴክኒክ ረገድ፣ የድራማውን ልቡ ምኑ ላይ ይሆን የሚለው የሀሳብ አይነት ጋር፣ የተዋናዮቹ የአልባሳት አለባበስ እና ትርጋሜ÷ በቦታዎች ውስጥ ያላቸው አቀመማጥ ትርጋሜን በሰም መንገድ ለማየት እንጥራለን፡፡መማረኬ ነው የሚያስሞነጭረኝ፡፡
በድህረ የስርጭት ዘመን (Post broadcast time) የቴሌቭዥን ተከታታይ ድራማዎች የመገናኛ ብዙኃን አይነተኛ መልክ ናቸው፡፡ በፕሮግራም ድልድል ውስጥ መቼ እና ምን አይነት መሆን እንዳለባቸው ሊሂቃንን የሚጋብዙ ጉዳዮች ሆነዋል፡፡ የቴሌቭዥን ጣቢያዎችም በተመልካቾቻው ላይ የገበያውን ድራሻ ለመውሰድ መፎካከሪያ የፕሮግራም አንቀፃች ናቸው፡፡ (audience and market share)
ለኢትዮጵያ ዘመኑ የቴሌቭዥን መሪነት የሚታይበትም ነው፡፡ በአይነት÷ በአላማም የተሰለፈው የቴሌቭዥን አይነት አየሩን ይዞታል፡፡ ዜናው፣ ፕሮግራሙ፣ ውይይቱ፣ ድራማው ይመረታል፡፡ (Daily production of the media houses) የቴሌቭዥን ተከታታይ ድራማዎች ደግሞ ተወዳጅ የቴሌቭዥን ሀሳብ ማቅረቢያ መሰፈሪያ ሁነዋል፡፡ (favorable television format for audience)
አብርሃም ገዛኸኝ÷ ሎሚ ሽታን ሳየው፣ የነገን አልወልድምን ስመለከተው ወደድኩት፡፡ ድራማ/ፊልም በድምፅ፣ በምስል አይነት፣ በተመጠነ ንግግር እንዴት አምሮ እንደሚገለፅ አሳይቶኛል፡፡ የቴሌቭዥን ድራማ/ ፊልም የሚወራ ሳይሆን የሚታይ እንደሆነ ደጋግሞ ሲያሳየን ለሙያዊ ውይይት እድል ይከፍታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መፅሀፍትን ወደ ቴሌቭዥን ድራማ/ፊልም ሲቀይር ስናይ ደግሞ ተደነቅን፡፡ ሎሚ ሽታ፣ የነገን አልወልድም እና የእግር እሳት ስራዎቹም ከመፅሀፍ የተወለዱ ናቸው፡፡ አድናቆታችን በደፈናው ከሚሆንም÷ ምክንያት አስቀምጠን መውደዳችንን መግለፅ ፈለግን፡፡
የእግር እሳት ገፀባህርያትን እና ዘመኑ፡-
ድራማው ሲጀምር የምንሰማው ቃል ጉዞ እንዳለብን ይነግረናል፡፡ ከገፀባህሪው ጋር አብረን ፈላጊዎች እንደሆንን ያሳየናል፡፡ የምፈልገውን ሰው አላውቀውም ይለናል፡፡ የጥያቄ እና የፍለጋ እስረኛ የሆነው ገፀባህሪ መንገደኛ÷ ሩቅ ተጋዥ እንደሆነ ጥቆማ ይሰጠናል፡፡ ተመልካቹንም ተዘጋጁ መንገዳችን ሩቅ ነው ይል ይመስላል፡፡ ፍለጋውን ሲጀምር÷ የቤቱን በር ከፍቶ ከሚወጣው መኪና ፊትለፊት የተዘጋ በር ያሳየናል፡፡ ፍለጋ የሚወጣው ግለሰብ ምን አይነት አድካሚ ጉዞ እንዳለው በሁለቱ የበር ወጎች/ ተምሳሌትነት/ ያመላክተናል፡፡ በተከፈተው በር÷ የተዘጋውን በር እያየን፡፡ አንተነህን (እዝራ አሰፋን) በዚህ መንገድ እንተዋወቀዋለን፡፡
የትዳር ህይወታቸው በልጅ ያልሞቀው የወይንዬ እና የደሬ ጎጆ አብይ ጉዳያቸው ምን እንደሆነ በነሱ ከማናገር ይልቅ በዙሪያቸው ካለ እውነት ጋር ሰፍቶ ሹክ ይለናል፡፡ በቴሌቭዥኑ ላይ የሚታየው የአራት ህፃናት መወለድ ጋር አስታኮ÷ የትዳራቸውን የልብ ጥያቄ ያቃምሰናል፡፡ ታሪኩም ከክፍል ክፍል የልጅ ነገር እሳት ሲሆንባቸው የበለጠ ለምን እንደሆነ ይገባናል፡፡ የሚስት አትኩሮታ እና የባል ወደ ኃላ ማለትንም ከምንተዋወቅበት ቅፅበት ጀምሮ የተገለጠ ነበር፡፡ እሳ በትኩረት ዜናውን ስታይ÷ በዜናው ውስጥ ራሳን የምታይ ሴት ሁና፣ ባል ደግሞ ከዜናው የሚሸሽበት መንገድ (የአይኑ ንግግር) አሳባቂ ሆኖ ይከሰታል፡፡ በዚህ ትዳር ውስጥ÷ ቴሌቭዥኑ የቤቱ መለያ ሆኖም ይቀጥላል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች በቤቱ ውስጥ የቴሌቭዥኑ ዜና፣ እግር ካስ ጨዋታ እና ሌሎችም ነገሮች በቤቱ ውስጥ ይደመጣል፡፡ ስለዚህም የነ ወይንዬ ቤት አንድ መለያ ድምፅ አድርጎልናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ገፀባህርያትን÷ ከገፀባህርያት በተለያዩ መንገዶች በመለየት ተመልካቹ ልብ እንዲል እድል ይሰጣል፡፡ (ውይ እነ እንትና ቤት ወሰደን ብሎ እንዲስብ ያደርገዋል፡፡ በድምፅ፣ በልብስ፣ በቦታ፣ በዘፈን ገፀባህሪያትን ለመለየት ይመከራልና፡፡
የድራማው ዘመን እና ያለውን መልክ ለማሳየትም ትንንሽ የሚመስሉ ጥቆማዎችን ያሳየናል፡፡ ይህ ድራማ አሁን ካለንበት ዘመን ጋር እንደተሳሰረም ለማሳየት የኢፌዴሪ ባንዲራን በፓሊሶቹ ቢሮ ውስጥ ያሳየናል፡፡ ዘመኑ መቼ እንደሆነም ጥቆማ ይሰጠናል፡፡ በዚህ ዘመን ውስጥ ያሉ ሰዎችንም ለማሳየት ሂዩማን ሄር ያደረጉ ሴቶች፣ ፅድት ያሉ የፓሊስ መኮንንኖች፣ አባራ የለበሰች መኪና፣ ሁለት መቶ ብር ለማውጣት የሚጠባበቅ ግለሰብን እና የታሰሩ የብር ኖቶችን በኪስ ከሚያጭቀው ግለሰብ ጋር አሰልፎ፣ የሚላስ የሚቀመስ በጠፋበት ቤት ፊታቸውን ኬክ የሚቀቡ ህፃናትን አስታኮ የዘመን ዥንጉርጉርነትን መልኩ ምን እንደሚመስል አይናችንን ለመግለጥ ይጥራል፡፡
የቴክኒክ እና የገለፃ ኃብታት በእግር እሳት ድራማ፡-
1. አሁን ያለንበት ዘመን Disorient እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ ድንግርግር ዘመን ውስጥ ደግሞ ለመኖር ትርጉም መፈለግ ያስፈልጋል፡፡ ድራማው ሲጀምር አስደንግጦን ነው ቀጣዮቹን ክፍል እንድንጠብቅ የሚያደርገን፡፡ ዋናው ገፀባህሪም ሚስቱን÷ ልጁን በሞት ተነጥቆ ነው የምናስተውለው፡፡ በዚህ አስደንጋጭ ገፅ ውስጥ ለመኖር ትርጋሜ ይፈልጋል፡፡ he is searching a meaning in the disorient circles. ከሞት ውስጥ ትርጉም የሚፈልግ ጎበዝ ነው፡፡ አባቱም÷ እናቱም ሲሞቱበት በተከታታይ እንደሆነ እንዳንዘነጋ፡፡ (በቀል ይሁን÷ ሌላ ተጨማሪ የህይወት እንክብል የሚያገኝበት መንገድን አብረን ከተጋዝን ከድራማው ጋር እየተገለጠልን ይሄዳል፡፡
ፕ/ር መሳይ ከበደ እንደሚሉት በድግግሞሽ ውስጥ የኢትዮጵያውያን የጊዜ እና የቦታ ኑባሬ ውስጥ ትርጉም መፈለግ የማያቃርጥ ነውም ይላሉና፡፡ ለመኖር ሲባል ከሞት ውስጥ ህይወትን ይሰራል፡፡ (Mirror approach with high intensity)
አብርሃም ገዛኸኝ አዳም ረታን በአንክሮ የሚያነብ የሚያደንቅ ስለሆነ÷ በምቾት አልባነት ውስጥ አላማን የሚሻ የጥበብ ዛር ይመስለኛል፡፡ በሀገር ቤትም ሞት፣ መሰደድ፣ መታረዝ፣ ህግ አልባነት፣ መረንነት በበዛበት ዘመን የድራማውን ታሪክ ከሞት ሲጀምር ለእኛ ለመኖር ትርጉም እንፈልግ የሚል ደውል ያቃጭልብኛል፡፡ ከመብከንከን ይልቅ ትርጉም መፈለግን፡፡ ዘመኑ እና የእግር እሳትም መንታ ሁነው ይታዩኛል፡፡ (ለምሳሌ ያህል አንድ ቃል ከዋናው ገፀባህሪ እንውሰድ÷ ልጄን ገደልኩት ብሎ ገዳዩን ይፈልጋል፡፡ ይህ ዲስኦርየንት የመሆን እና የሚያቃትት ትርጉም ፍለጋን በአግባቡ ያሳያል፡፡
2. በከባቢያዊ ገፀባህርያት አማካኝነት ዋና ገፀባህሪውን በሀሳብ፣ በኑሮ ይደግፈዋል፡፡ መንገደኛ የሆኑትን ገፀባህርያት እርባና ያላቸውን መሆኑን የምናውቀው ዋናውን ገፀባህርያት ከእንቅልፉ ሲያነቁት፣ ከሀሳብ ማጣት ወደ ሀሳብ ባለቤትነት ሲያሻግሩት ነው፡፡ ዋናው ገፀባህሪን ሰው አድርጎ ያስቀምጥልናልም፡፡ ልዕለ ሰብ አያደርግብንም፡፡ ለምሳሌ የልጁን ገዳይ በሚፈልግበት ወቅት ቀኑን፣ ሁኔታው ምን እንደሚመስል የሚያውቀው ከባለ ሱቅ ሻጮቹ መንገደኛ ወሬ ነው፣ ፓሊሶቹ የተራበውን ፍትህ በፍጥነት ስላልሰጡት÷ ፍትህን በቶሎ የማገኝ ከሆነ ከራስ በላይ ፍትህ የሚሰጥ÷ ፍትህን የሚፈልግ የለም የሚለው ሀሳብ የሚያገኘው ከመጠጥ ቤት አዘውታሪ ሰዎች ነው፡፡ ዋናው ገፀባህሪ ቆሞ እንዲጋዝ ትኩረት ባልሰጠናቸው መንገደኞች እና ተቀማጮች ገባር ሁነው÷ ዋና ገፀባህሪውን ወንዝ ያደርጉታል፡፡ (በተናቁት ቁመን የምንጋዝ ክቡራን ሆይ ይላል፡፡ አብዘርድ ነው በእውነት፡፡ (the insignificant dwell purposely.)
3. የእነ ወይንዬ ትዳር በልጅ የተባረከ ባለመሆኑ ወይንዬ መፍትሄ ፍለጋው ላይ ትበረታለች፡፡ በሀኪም ቤት ውስጥ ፈውስ ለማግኘት በነበራቸው የህክምና ሂደት ውስጥ የወይንዬ ብርታት በአቀማመጣቸው ያሳዩናል፡፡ ወይንዬ ከፊት ቀድማ፣ በአንክሮ ትከታተላለች፤ የታከተው ባለቤታ ደግሞ በመሰላቸት ተቀምጦ ከኃሏዋ ተሰልፋል፡፡ (the physical message tells beyond what is heard) ከዚህም በተጨማሪ ወይንዬ ልጅ ለማግኘት ከአለቃዋ ቤት በተገኘች ጊዜ÷ የሀሳብ ሙግት ከአለቃዋ ይገጥማታል፡፡ ልጅ እኮ የሚገኘው በተቀደሰው መንገድ ብቻ ሳይሆን÷ ከትዳራ ውጪም ማግኘት እንደምትችል በልስላሴ ይነግራታል፡፡
ዳይሬክተሮቹ በእጅ መታጠቢያ ውስጥ ያለውን መስታወት አንድ ወይንዬን አቁመው፣ በአካል ያለችውን ወይንዬ ሁለት አድርገው አለቃዋን ደግሞ ሶስተኛ ሰው በማድረግ የሶስትዮሽ ቃለ ተውኔት ያሳዩናል፡፡ የወይንዬ ኩፋሌ ነብስንም ምን ያህል አስጨናቂ እንደሆነ እንድናበክረው ያስገድዱናል፡፡ (Triangular dialogues) ባለትዳሮቹ በትዳራቸው ውስጥ ያለውን የልጅ ጥያቄ ጎጆውን እየነቀነቀው እንደሆነም ካሜራውን ባልተረጋጋ ቀረፃ ውስጥ ያደርጉታል፡፡ (Camera jarring with intents)
4. አንተነህ ወደ እዝራ በሚቀየርበት ሁኔታ ውስጥ የብርሃን አጠቃቀማቸው እና የቦታ ንግግራቸው የተወደደ ነው፡፡ የብዕር ስሙን ማንነቱ ሲያደርገው አንተነህ ይኖርበት የነበረውን ቤት ጭምር ትቶ÷ ብርሃን የነበረበትን ቦታ ጨለማ አድርገው ቀጣይ ጉዞውን (እዝራነቱን) ብርሃን ያበሩበታል፡፡ በአንድ ሰው አማካኝነትም ሁለት ገፀባህርያትን ያለብሱልናል፡፡ (dual personality) (አንድ ሰው ስንት ነው÷ አንድም ብዙም፡፡
5. ልጅ የማግኘት ጥያቄአቸውን ምን መልክ እንዳለው በሀኪሙ ጀባ ከተባሉ ብኃላ ወይንዬ እና ባለቤታ በዝምታ ይጋዛሉ፡፡ ከዝምታቸው ጀርባ ልጃን የምታጠባ የእናት ስእል ይታያል፡፡ (The director talks in the circle of silence)
6. ገፀባህርያቱ ብዙ ጊዜ ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፡፡ የዚህ ቀለም አንድምታውም÷ ገፀባህርያቱ ለሚከውኑት ነገር የሚሰጡትን ትኩረት አሳይ ነው ይባላል፡፡
7. በድራማው ውስጥ የመፅሀፍ ክምሮች ይታዩናል፡፡ ከመፅሀፎች ውስጥ ግን የተቆለፈበት ቁልፍ እና ዶም ያዘለ ዶሴ የሚሉት መፅሀፍት በጉልህ ይታያሉ፡፡ ለምን ብለን ብንጠይቅ÷ የድራማው ታሪክ ደም የወለደው ዶሴ ነው÷ ቁልፉን ለማግኘት ጉዞ ላይ እንደሆነ በገደምዳሜው ይነግረናል፡፡ (they build the sequences and details with purpose, all staff are constructed with roles.)
ሐገረ-ሰባዊ ሰምና ወርቆች በእግር እሳት ድራማ ውስጥ፡-
1. አንተነህ የልጁን የትምህርት ቤት ክፍያ አስመልክቶ ተማሪ ቤት በተጠራበት ጊዜ÷ እግሩን ከመሬት ጋር እየመታ ይጠብቃል፡፡ እግሩን ከመሬቱ ጋር ሲመታ ምን ያህል ጭንቀት ውስጥ እንዳለ ማሳያ ነው፡፡ (ግድ ጨንቆኛል ማለት አይጠበቅበትም፡፡
2. የህፃኑን የልዑል ሞት ለማርዳት÷ በቤት እና ከቤት ውጪ ያለውን ወግ የማህበረሰባዊ ህጋችንን ያሳየናል፡፡ በወግ በማዕረግ መርዶው ይነገራል፡፡
3. የነ ወይንዬ ትዳር በቤተሰቦቻ፣ በስራ ባልደረቦቻ ጣልቃ ይገባበታል፡፡ በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ ትዳር የባለትዳሮቹ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ ያሳየናል፡፡ ታሪኩን በዚህ መንገድ ማሳየቱ ለተመልካቹ እንዲቀርብ፤ እንዲረዳው ያደርገዋል፡፡ (The meaning of communal life’s)
4. በየካ ጫካ ውስጥ ሬሳ ለመጣል የማይዘገንናቸው ገፀባህርያት አይተናል፡፡ ይህንን ዱብ እዳ ከማሳየቱ በፊት በድምፅ አማካኝነት ክፉ ነገር ሊሆን እንደሆነ ይነግረናል፡፡ የውሻዎቹ ማላዘን፣ የእንቁራሪቶቹ ማንቃረር አንድ ክፉ ነገር እየመጣ እንደሆነ ቀድመን እንድንገምት ያደርገናል፡፡ (the audience is part of the drama; we have a role in it.)
5. አባት አንተነህ በህልሙ ልጁን ያየዋል፡፡ ህልም በሀገራችን ፍትህ ያላገኘ ወይንም ነብሱ ያላረፈን ሰው ማመልከቻ ወካይ ሆኖ ይሳላል፡፡ ደመ ከልብ የሆነው ልዕል÷ አባቱ ከፍትህ ፍለጋው እንዳይዘነጋ በህልሙ ይከሰታል፡፡ ልጅም÷ ንፅህ ነብስም ስለሆነ ነጭ አልብሶ ያናግረዋል፡፡ በግብር የሚካትንበትን እውነት÷ በህልም ያሳየዋል፡፡ ያነቃዋል፡፡ (the fulfillment daily desire)
6. ፍትህን ፍለጋ ማንነትን ቀይሮ፣ መልክን ለውጦ፣ አካልን ቀይሮ ፍትህን በራስ ለማግኘት በባህላችን የነበረ÷ ያለ ነው፡፡ አንተነህነቱን ክዶ እዝራ መሆንም በሀገራችን የኖረ÷ የምንኖርበት ነው፡፡
7. በገፀባህርያቱ ውስጥ ሀገራዊ የቋንቋ የንግግር አረፍተ ነገሮችን በብዙ ሰምተናል፡፡ ለምሳሌ ያህል ጀርባዬ ነግሮኝ ነበር፣ ልጆቹን ለምን ባህር ዛፍ አላጠንሻቸውም እና የመሳሰሉትን ማስታወስ ይቻላል፡፡
የእግር እሳት ወርቅ፡-
እስካሁን በእግር እሳት ተከታታይ ድራማ ውስጥ ያየናቸው ገፀባህርያት ዳይሬክተሩ እስትንፋስ ሰጥቶአቸው ህይወታቸውን የሚኖሩ ይመስላሉ፡፡ ስጋቸውም÷ ነብሳቸው በአንድ ሰምሮ ደስ ብሎናል፡፡በእግር እሳት ድራማ በተለያዩ ቤተሰቦች ውስጥ የልጅ ጉዳይ አንገብጋቢው ነው፡፡
የልጁን ሞት በፍትህ ለመካስ የሚሮጥ አባት አንዱ ነው፣ የትዳራቸው እድል ፈንታ በልጅ ላይ የተንጠለጠለ÷ በቀጭን ክር ላይ የቆመም ትዳር አለ፣ የቤተሰባቸው ብቸኛ መተዳደሪያ የሚመስለውን የቤት ኪራይ ኑሮ ላይ የሚወስነው ልጅ ቤትም አይተናል፣ በልጆቻቸው ልጆች ደስ የተሰኙ አያት ነገር ግን የመጀመሪያ ልጃቸው ልጅ ስላልወለደች የሚነዘንዙ እናትም አስተውለናል፡፡
በእግር እሳት ድራማውስጥ ልጅ የህይወታቸው ቀዳሚ መቅድም ሁናል፡፡ የደስታቸው፣ የሀዘናቸው ምክንያትም ነው፡፡ ለልጅ ሲባል ብዙ እየሆኑ ነው፡፡ ልጅ ሊያገኙ፣ ልጅ ካልሰራን የሚሉ ሰዎች፣ ቤቶች ሞልተዋል፡፡ ነጠላው ትርጋሜ ይህ ነው፡፡
ወርቁ ላይ እንምጣ፡-
ዘመኑ ግራ የገባው ነው ብለናል፡፡ በዚህ መልክ አልባ ዘመን ውስጥ ሀገር በልጆቻ እያዘነች በየቀኑ ደም ታነባለች፣ ህይወት ግን ወንዝ ነውና ከደዌዋ እንዲፈውሳት ከአለም አብራክም ሆነ÷ ከሰማይ ደጅ ልጅ ለማግኘት ከቤተእምነቱ÷ ከሳይንሱ አለም ትባክናለች፡፡ መዳን እና ተስፋዋ በልጃ ላይ ሁኖ፡፡ ጉረምሳ፣ ሽማግሌ ልጆቻ ምጥ የሆኑባት ሐገር፤ ጎሎጎታን አልፋ ትንሳኤዋ እንዲሆን ልጅ ልትሰራ፤ እልልታ ልታሰማ ምጥ ላይ ነች፡፡

Source: Habtu Girma Fetaw


Comments

or to write a comment

Latest News and Articles

Ethiopian movie news and article - Asansiro
read more