Feb. 29, 2020, 2:22 p.m. by EtMDB
የፈረንሳዩ የቴሌቪዥን ድርጅት ካናል + ኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን ቻናል ከፍቶ ፊልሞችን ለማሳየት የሚያስችለውን ስምምነት ከድርጅታቸው ጋር መፈራረሙን የኖላዊ ፊልም ፕሮዳክሽን ሥራ አስኪያጅ ሐኒ ወርቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።የኢትዮጵያ ፊልም ፕሮዲውሰሮች ማህበር ሰብሳቢ የሆኑት ቢንያም አለማየሁ በበኩላቸው፣ ካናል ፕሉስ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የውጪ ድርጅቶችም የኢትዮጵያን ፊልሞች ለማሳየት ፍላጎት ኖሯቸው ወደ ማህበራቸው መምጣታቸውን ይናገራሉ። የሚከፈተው ቻናል የተመረጡ የኢትዮጵያ ፊልሞች ብቻ የሚታዩበት መሆኑን የሚናገሩት ሥራ አስኪያጇ፤ ለተወሰኑ ወራት አዳዲስ ፊልሞችን በመከራየት ለማሳየት መስማማታቸውን ገልፀዋል። ሥምምነቱ የተለያዩ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ መሆኑን የገለፁት ሥራ አስኪያጇ፤ ከፕሮዲውሰር ማኅበር ጋር በመሆን የሚታዩ ፊልሞችን የመምረጥ ሥራው እንደሚሠራ አስታውቀዋል። ካናል ፕሉስ፣ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሰሩ ፊልሞችን ብቻ ለተወሰነ ጊዜ ለማሳየት መዋዋሉን የሚገልፁት አቶ ቢንያም፣ የሲኒማ ጊዜያቸውን ጨርሰው የወረዱ አዳዲስ ፊልሞች፣ ሌሎች የማሳያ አማራጮችን (እንደ ዩቱብ ያሉን) ከመጠቀማቸው በፊት በቴሌቪዥን የሚቀርቡ መሆኑን ያስረዳሉ። • የ'ፍሬንድስ' ፊልም ተዋናዮች እንደገና ቢመለሱስ? • "ምን ልታዘዝ አልተቋረጠም" ፋና ብሮድካስቲንግ ሐኒ እንደሚሉት ይህ ስምምነት የፊልም ፕሮዲውሰሮችን እንዲሁም በፊልም ሥራ ላይ የተሳተፉ አካላትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስረድተዋል። "የሚታዩት ፊልሞች የሃገራችንን ገጽታ የሚገነቡ፣ ፊልሙ የደረሰበትን ደረጃ የሚያሳዩ ይሆናሉ" ያሉት ሥራ አስኪያጇ፤ ቻናሉ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ፊልም ብቻ እንደሚያሳይ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ፊልሞች ገቢያቸውን የሚሰበስቡት በአብዛኛው በሲኒማ ቤቶች ከሚያሳዩት ነው የሚሉት የኖላዊ ፊልም ፕሮዳክሽን ሥራ አስኪያጅ፣ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲገዙም በርካሽ ዋጋ ነበር ይላሉ። ሥራ አስኪያጇ አክለውም እነዚህ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እስከዛሬ ድረስ ፊልሞቹን ሲገዙ የባለቤትነት መብቱንም አብረው እንደሚወስዱ አስታውሰው፤ ተጠቃሚ አላደረገንም በማለት የነበረውን ክፍተት ያስረዳሉ። ካናል ፕሉስ ግን ከዚህ በተለየ አዳዲስ ፊልሞችን ለስድስት ወር ብቻ የማሳየት ፈቃድ እንደሚወስድ አስረድተው የተሻለ ክፍያም ይከፍላል ብለዋል። ከስድስት ወር በኋላ ፕሮዲውሰሩ ለፈለገው ጣቢያ የመሸጥ መብት ይኖረዋል ያሉት ሥራ አስኪያጇ "ይህንን ማስጠበቅ መቻል ትልቅ ድል ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ፊልሞች በተለያየ መንገድ እንደሚሸጡ ያስታወሱት ሐኒ፤ በሲኒማ ቤቶች ማሳየት፣ በኦንላይን እንዲታይ ማድረግና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለተወሰነ ጊዜ መብቱን ወስደው እንዲያሳዩ ማድረግ እንደሚገኙባቸው አስረድተዋል። ይህ ሥምምነት ሁለት ዓመት መፍጀቱን የሚናገሩት አቶ ቢኒያም በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያን ፊልሞች ለኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ለማሳየት ፈልገው መምጣታቸውን ይናገራሉ። ፊልም በተለያየ መንገድ ሊሸጥ ይችላል የሚሉት አቶ ቢኒያም፣ ከሲኒማ ቤት ውጪ፣ በሲዲ፣ በዩቱብ፣ በቴሌቪዥን በመሸጥ መጠቀም እንደሚቻል ያስረዳሉ። የካናል ፕሉስም መምጣት ፊልም ሠሪዎቹ የተሻለ ገንዘብ ለማግኘት የሚያስችል በመሆኑ "እንደ ፕሮዲውሰር ብቻ ሳይሆን እንደ ባለሙያም ትልቅ አቅም ይፈጥራል" ሲሉ ይናገራሉ። ከዚህ በፊት ባለቤትነታቸውን አሳልፈው የተሸጡ ፊልሞች በጣቢያቸው እንደማይታዩ የሚገልፁት የኖላዊ ሥራ አስኪያጅ፤ ነገር ግን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ በተለያዩ ጣቢያዎች ሲታዩ የነበሩ ካሉ ኮንትራታቸውን ከጨረሱ በጣቢያው ሊታዩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። ካናል ፕሉስ በኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን ቻናል ሲከፍት ኢትዮጵያዊ ስም የሚኖረው ሲሆን፤ ስምምነቱ በቴሌቪዥን ማሳየት ብቻ እንጂ ኦንላይን ሥርጭቱን እንደማይመለከተው ገልፀዋል። ኖላዊ ፊልም ፕሮዳክሽን ከተመሠረተ 10 ዓመት የሆነው ሲሆን የተለያዩ ፊልሞችንና ዘጋቢ ፊልሞችን በመሥራት ይታወቃል። ፕሮዳክሽኑ እንደ 'ይግባኝ' ያሉ ፊልሞችን ፕሮዲውስ በማድረግ ለሕዝብ ዕይታ ማብቃቱ ይታወሳል። ካናል ፕሉስ ተቀማጭነቱን በፈረንሳይ ያደረገ የሚዲያ ተቋም ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ20 ሚሊየን በላይ ተከታዮች አሉት። • የኢትዮጵያ ፊልም ወዲያና ወዲህ ካናል ፕሉስ፣ የሚዲያ እና የፊልም ኩባንያ ለኢትዮጵያ ገበያ የሳተላይት የቴሌቪዥን አገልግሎቶችን በመስጠትና ፊልሞችን ፕሮድዩስ በማድረግ ከ70 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ኢንቨስት እያደረገ ነው ሲሉ በፈረንሳይ ኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ሔኖክ ተፈራ ሻውል በሊንክዲን ገጻቸው ላይ አስታውቀው ነበር። አምባሳደሩ ድርጅቱ ያደረገውን ስምምነት "ለአገራችን የባህል ኢንዱስትሪ ልማት የላቀ አስተዋፅዖ ይኖረዋል" ሲሉ ነበር የገለፁት። የፊልም ፕሮዲውሰሮችም ሆነ ሠሪዎች በዚህ ሥምምነት ደስተኛ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ቢኒያም፣ በዚህ ዓመት መጨረሻ አስፈላጊውን ዝግጅት ጨርሶ ማሳየት ይጀምራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።
source: BBC Amharic
July 28, 2020, 9:17 a.m.