Meba (መባ ፊልም ኪሳራችን በጊዜና በገንዘብ ብቻ የሚለካ አይደለም )

ትላንት እንደው በስህተት ልበለው መሰል እግሬ እንዳመራኝ በቅርቡ የተመረቀውን ‘መባ’ ፊልም ለማየት ወደ አንዱ ሲኒማ ቤት ጎራ ማለት….ምክንያት ነበረኝ፡፡ ‘ረቡኒ’ የተባለውን ፊልም ካየሁ በኋላ ሀገርኛው ስሜት ይበልጥ ያየለበት ፊልም ከመሆኑ አንጻር በተለይም እንደ ፊልም አብዛኛውን element የያዘ በመሆኑ በነካ እጅ ብዬ የዚሁ የረቡኒ ደራሲ የደረሰችውን መባ ፊልም ማየት … ውስጤ የቀረ ነገር በመኖሩና በረቡኒ የትዝታ ቀዳዳ ውስጥ እንደማጮለቅ መስሎ ስለታየኝም ጭምር ነበር፡፡

በህይወታችን እንደዚህ አይነት የስሜት ግጭቶች ፈትነውን ያውቁ ይሆናል፡፡ ልክ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ከፍቅር እስከ መቃብር ወዲያ ለአሳር እንደተባሉት አይነት፡፡በርካቶች የትላንት የጽሁፍ ትሩፋታቸውን መድገም አልቻሉም፡፡ ‘መባ’ ፊልም ይሁን ምን ይሁን ጭብጡ እንኳ ሳይገባኝ (እርግጥ ነው ፊልሙን መጨረስ አቅቶኝ አቋርጬ ብወጣም) በተለያዩ ሃሰቦች ስንላጋ ፣ ምክንያታዊነት ባጣንላቸው ግጭቶች ውሰጥ ስንቧቸር ፣ በዋና ገጸባህሪያት አቅምና ሀይል ማጣት ‘ምንደግፍበት አጥተን ስንቸገር ፤ ያም ብቻ አይደለም …. ዋና ገጸ ባህሪው the center of the story ሆኖ ሳለ ምንም ሳይሰራ፣ ምንም ሳይፈጥር ጭራሽ በደራሲዋ ተገድሎ ሚናውን በአግባቡ ሳይወጣ ከፊልሙ ታሪክ ሲሰናበት ማየት የእውነት ⷐረ የጸሀፊያን ያለ ያስብላል፡፡ ሌላው ፊልሙን እያየሁ ከዓመታት በፊት ያየኌቸውን የ Richard Gere ‘ Mr Jones” በ1993 እ.ኤ.አ የተሰራውን እንዲሁም በ1998 እ.ኤ.አ Robin Williams የሰራው ‘Patch Adams” ፊልሞችን ይበልጥ እንዳስታውስ አድርጎኝ ነበር፡፡ የታሪክ መወራረስ ወይስ የሃሳብ ስርቆሽ ወይስ ….. ትቸዋለሁ፡፡

የገጸባህሪያት አወቃቀር ላይ ጠንካራ፣ ለሙያቸው ብሎም ለሙያው ስነምግባር የተገዙ፣ ጽኑ የመሰሉ የስነአዕምሮ ሀኪሞች (በ dialogue የተነገሩን) ፊልሙ ላይ ግን የገዛ በሽተኞቻቸውን የሚቆጡና የሚያሽቆጠቁጡ ሲላቸው በጥፊ የሚማቱ ሆነው ሲሳሉ ማየት ይገርማል፡፡ ባይነገረንም በአእምሮ ህሙማን ላይ እጅ ማንሳቱ ጥያቄ የሚፈጥር ይመስለኛል፡፡ ምናልባትም ለጸረ-ሙስና የቤትስራ ለመስጠት ካልሆነ በስተቀር….ሙያቸው ሳይሆን ሙያተኛ መስለው የተቀጠሩትን ለማጥራት፡፡

ከምንም በላይ …ከምንም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ከነበሩበት ይዘት በመለየት በታሪክ ውስጥ መጠቀም…ይህ እንኳ ባይከፋም ለምንና እንዴት እንደምንጠቀምባቸው አለማወቅ ግን ድፍረት ነው፡፡ ይሄንን አካሄድ ረቡኒ ፊልም ላይ ባየውም ብዙም ሳይጎረብጠኝ ነበር ያለፈው…ነገር ግን መባ ላይ ግን በእኔ አተያይ ከድፍረትም የዘለለ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በተለይ የመልከጼዴቅ ታሪክ የቅዱስ ኤልያስና የቅዱስ ጳውሎስ ታሪክ (ስማቸው ሳይጠቀስ ግን ግብራቸውን በማንሳት)….በረቡኒ ታሪክ ዮቶር ለምን ዮቶር እንደተባሉ የሚገባኝ እውነት አለ፡፡ የታላቁ ሙሴ ሚስት አባት የነበረው ኢትዮጵያዊው ዮቶር በአስተዳደር ና አመራር ላይ ያለውን ክህሎት ለሙሴ በብቃት በማስተማርና በማውረስ ሃይማኖታዊም ኢትዮጵያዊነትንም ያንጸባረቀ ታሪክ ለዚህኛውም ትውልድ ማውረስ እንደሆነ ሳይዘልቀኝ አልቀረም፡፡ መልከጼዴቅ የሚለው ስምና ገጸባህሪይ ሲመጣ ግን ቆም ብለን እንድናስብ የሚያግዘን ይሆናል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል፡፡ መልከጼዴቅ ካህን የመጀመሪያው ካህን፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ በብዙ መልክ ቤተክርስቲያን የምታመሰጥረው መልከጼዴቅ… እንደው እንደዘበት ታሪክ ውስጥ ተሞጅሮ ማየቴ በጣም ቢያሳዝነኝም አርቲስቱን ግን ነፍሳቸውን ይማርና ከማድነቅ ወደኋላ ማለት አልፈልግም፡፡

በተረፈ ፊልሙን ለማየት ነጠላ አጣፍታችሁ እንድትመጡ የሚል የአለባበስ ፕሮቶኮል ማስነገር እስኪቀረው ድረስ ስብከት የበዛው የመባ ፊልም ጽሁፍ …ምናልባትም ከረቡኒ በዝቶ የተረፈ ነው ብል ድፍረት እንዳይሆንብኝ፡፡
ነገር ግን ፊልሙ ላይ እንደ ቅመም በተን በተን የተደረጉ ረዳት ተዋንያን (ሴቶቹም ወንዶቹም) ፊልሙ ነፍስ ሳይኖረው ነፍስ ያለው እንዲመስል ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ አዝናኞቻችን እነሱ ብቻ ነበሩ፡፡ ለማንኛውም የዚህ ሃሳብ እና የፊልሙ ፍፃሜ አቋርጦ በመውጣት የተደመደመ በመሆኑ እኔም ሆንኩ ፊልሙን አቋርጠው የወጡ ሁሉ ኪሳራችን በጊዜና በገንዘብ ብቻ የሚለካ አለመሆኑን መናገር ግን እፈልጋለሁ፡፡

By Tigist Kassa


Comments

or to write a comment

Latest News and Articles

Ethiopian movie news and article - Asansiro
read more