Aug. 28, 2016, 7:02 p.m. by EtMDB
አርቲስት ሚካኤል ታምሬ የመዝናኛ አምድ እንግዳችን በጣም ዘግይቶም ቢሆን “የሚስት ያለህ” እና “ጓደኛሞቹ” ቴአትርን ሰርቷል። በቲቪ ከሰራቸው ድራማዎች “ዋናው ስራ አስኪያጅ” እና “በርባን” የተሰኘውን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅነት ያገኘበትን “ዳና” የተሰኘ የቴሌቭዥን ድራማ ላይም በመስራት ላይ ይገኛል። በፊልሙ ረገድ ቁጥራቸው የበረከተ ቢሆንም ለማስታወስ ያህል “ሚዜዎቹ”፣ “ሔሮሺማ” “ነቄ ትውልድ”፣ “ነውጥ”፣ በዚህ ሳምንት፣ በቅርቡ ደግሞ “ባጣቆዩኝ” የተሰኘውን ፊልም ጨምሮ ከ20 ያላነሱ ፊልሞችን ሰርቷል። እንግዳችን አርቲስት ሚካኤል ታምሬ ይባላል።
አርቲስት ሚካኤል ታምሬ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ብሉናይል ፊልም አካዳሚም ተቋም ውስጥ በመግባት ስለፊልም አፃፃፍና ቴክኒክ በተለየ ትኩረት ሰጥቶ የተማረ ባለሙያ ነው። ከሚካኤል ጋር የነበረን ቆይታ በዚህ መልኩ አስተናግደነዋል።
ሰንደቅ፡- በፕሮፌሽናል መድረክ ቴአትርን የሰራኸው ትምህርትህን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ካጠናቀክ ከ10 ዓመታት በኋላ ነው፤ አልዘገየህም?
ሚካኤል፡- ዘግይቻለሁ። ተመርቄ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራሁት “የሚስት ያለህ” ቴአትርን በብሔራዊ ቴአትር ነው። ምንድ ነው መሰለህ ከተመረኩኝ በኋላ ከጓደኞቼ ጋር ሆነን የቴአትር ኢንተርፕራይዝ አቋቁመን ስራዎችን እንሰራ ነበር። በብዛት እንሰራቸው የነበሩት ስራዎች ከNGO ጋር የተያያዙ ናቸው። ይህም ቴአትር ለማህበራዊ ፋይዳም መዋል ይችላል በሚል መነሻነት ነው። ሌላው ምክንያታችን ግን በቴአትር ቤት ከመቀጠር ውጪ ስራም መስራት ስለነበረብን ነው በግላችን መስራትን የመረጥነው። እንደምታውቀው አገሪቷ ውስጥ ያሉት ቴአትር ቤቶች አራት ናቸው። በሳምንት ውስጥ ያሉት ቀናት ደግሞ ሰባት ናቸው። በእነዚህ ቀናት ውስጥ ሁላችንም መድረክ አግኝተን ለመስራት ጊዜ ያስፈልገን ስለነበር ያንን ጠብቄያለሁ። ሌላኛው የዘገየሁበት ምክንያት ደግሞ ሰዎች ችሎታዬን አምነውበት እስኪጠሩኝ ነበር፤ አሰሩኝ ብዬ ገፍቼ መሄድ አልፈልግም ነበር። ምናልባትም ችሎታው የምር ካለኝ አንድ ወቅት ላይ መውጣቴ አይቀርም ብዬ አስብ ስለነበረ ይሆናል። አንዳንዴ መዘግየቴን ሳስበው ምን ይሰማኝ እንደነበር ታውቃለህ? በቃ ቴአትር ቤት ሳልሰራ ላረጅ ነው እንዴ? ብዬ ሁሉ ራሴን የጠየኩበት አጋጣሚ ነበረ።
ሰንደቅ፡- ዘግይተህም ቢሆን ጥሩ የመድረክ ስራዎች አጋጥመውሃል ማለት ይቻላል?
ሚካኤል፡- አዎ! ጥሩነቱ ምንድው አብሬያቸው የሰራዋቸው ሰዎች በጣም ስም ያላቸውና አንጋፎች መሆናቸው ነው። ቴአትሮቹ “የሚስት ያለህ” እና “ጓደኛሞቹ” ሲሆኑ፤ ሽመልስ አበራ (ጆሮ)፣ ፈለቀ የሚውሃ አበበ፣ አዜብ ወርቁ፣ ሸዋፈራሁ ደሳለኝ፣ ገነት አጥላው፣ መኮንን ላዕከ፣ ሰብለ ተፈራ እና ሚኪ ተስፋዬ አሉ። ይህን ስታይ መታገሴን በጣም ነው የወደድኩት፤ እድለኛም ነኝ።
ሰንደቅ፡- ጓደኛሞቹን አንተ ልጅ እያለህ አይተህው ስትመኘው የነበረውን ገፀ-ባህሪ ነው የሰራኸው?
ሚካኤል፡- አይደለም። ያኔ የተመኘሁትና የወደድኩት አለማየሁ ታደሰ ይጫወተው የነበረውን ገፀ-ባህሪይ ነበር። ነገር ግን ተክለ ሰውነታችን አይገናኝም። እርሱ ቀልጣፋና ፈጣን ሲሆን እኔ ደግሞ ለዛ ገፀ-ባህሪይ የሚሆን አቋም አልነበረኝም። በመሆኑም ሌላ ገፀ-ባህሪ ነው የሰራሁት። “ጓደኛሞቹ” ቴአትር ላይ መስራቴ በራሱ ለኔ ትልቅ ደስታ ነበር የፈጠረልኝ።
ሰንደቅ፡- ቴአትር መስራት የተለየ የሚፈጥረው ስሜት አለ?
ሚካኤል፡- አዎ ይሄን እኔ ላረጋግጥልህ እችላለሁ። ሁለቱን ቴአትሮች (የሚስት ያለህን እና ጓደኛሞቹን) በሰራውባቸው ሶስት አመታት ውስጥ ወደቴአትር ቤቶቹ ስሄድ ውስጤን በጣም ደስ እያለው ነበር። ያን ያህል ደስተኛ መሆኔን ሳስበው ቴአትር መማሬ ትክክል እንደነበር ይሰማኛል።
ሰንደቅ፡- ቀድመህ በቲቪ እና በፊልም ስራዎችህ መታወቅህ ምንአለ? በቴአትር ቢሆን የሚያስብል ቁጭት ይፈጥርብሃል?
ሚካኤል፡- ያኔም ቢሆን ጊዜ አለኝ ብዬ አስብ ነበር። ቴአትር ከዚህ በኋላም ቢሆን መስራቴ አይቀርም። ሌላው ነገር የቴአትር ዳይሬክተሮችም መስራት እንደምችል ያዩ ይመስለኛል። ስለዚህ ወደፊት በመስራት አካክሰዋለሁ። በዚህ ላይ በቅርቡ ለመድረክ የሚበቁ ቴአትሮችን እያጠናሁ ስለሆነ በደንብ እመጣለሁ።
ሰንደቅ፡- ከፊልም ስራዎችህ ግንባር ቀደሙ “ሚዜዎቹ” እንደሆነ ተናግረሃል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የራስህን ስራ በስክሪን ስታየው ምን ተሰማህ?
ሚካኤል፡- እውነቱን ለመናገር እርግጠኛ አልነበርኩም። ጥሩ ይሆናል አይሆንም ብሎ መወሰን አልቻኩም። ነገር ግን ስሰራ ዳይሬክተሩ በጣም ደስተኛ ነበር። ከዚያ ሰውም ቢወደው ጥሩ ነው እያልኩ፤ ሲኒማ ቤት ተደብቄ አንድ ሁለቴ አየሁት፤ ጥሩ ነበር። ከዚያ በኋላ የሰራሁት ከሰራዊት ፍቅሬ ጋር “ሔሮሺማ” ፊልምን ነው። በጣም ጥሩ ስራ ነው ከሁሉም በላይ ደግሞ ከትላልቅ ተዋንያን ጋር ነበር የሰራሁት። እነአበበ ባልቻ፣ ሰራዊት ፍቅሬ፣ ሙሉዓለም ታደሰና መሰረት መብራቴ የሚያካክሉ አንጋፋ ተዋንያኖች ነበሩበት። አንደኛ ነገር ከእነዚህ ትልቅ አክተሮች ጋር መስራቱ በራሱ ለኔ ትልቅ ነገር ነው። ሌላው ነገር ግን ከእነዚህ ሰዎች ጋር አብረህ ገብተህ ልክህን ማወቅህም በጣም ጥሩ ነው።
ሰንደቅ፡- ባንተ እይታ የኢትዮጵያ ፊልም ሂደት ምን ይመስላል?
ሚካኤል፡- ከቁጥር አንፃር እድገቱ አለ። ነገር ግን አሁን-አሁን አንድ እያሳሰበኝ የመጣው ነገር ምን መሰለህ? አንድ ቀሽም ፊልም በወጣ ቁጥር ሰዎች ከዚህ የተሻለ ፊልም መስራት እንችላለን የሚል ድፍረት እያገኙ ይመስለኛል። ምክንያቱም ከዕለት ወደዕለት የማያቸው የፊልም ፅሁፎችና ቴክኒካቸው በጣም የደከሙ ናቸው። አንድ ፊልም 70 እና 80 ገጽ ተፅፎ ስታነበው ምንም ጠብ የሚል ፍሬ ነገር የለውም። እና ለምን ተጻፈ ብዬ ስጠይቅ ደፋሮች እየተበራከቱ እንዲመጡ ይነግረኛል።
ይህ ትልቁ ፍርሃቴ ነው። ይህ ፍርሃቴ ደግሞ የሚመነጨው ከምን መሰለህ?እኛ እንደፊልም ሰሪ እንጀራችን ተመልካቹ ነው። ተመልካቹ እስካለ ብቻ ነው ፊልሙን እየሰራን መኖር የምንችለው። ይህ ተመልካች ሸሽቶን ወደቤቱ እንዲገባ ካደረግነው የኛ ነገርም አደጋ ውስጥ ይገባል ማለት ነው። ባይገርም የፊልም “ኮርስ” ሊሰጡን ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከደቡብ አፍሪካም ሰዎች መጥተው ነበር። በጣም የሚገረሙበት ነገር ተመልካቹን ነው። የሆሊውድ ፊልም እያለ የእናንተን ፊልም ለማየት ሰው ተሰልፎ ይቆማል? ሲሉ ተደንቀው ነው የሚጠይቁን። አውሮፓ ውስጥ መንግስት ስለሚደጉማቸው እንጂ ፊልም ተሰርቶ ገበያው አያዋጣም። ሌላው ኬኒያን ውሰድ እነርሱ በብዛት የሚያዩት የምዕራባውያኑን ስራ ነው። የራሳቸውን ስራ ለማሳየት ያሉት ሲኒማ ቤቶች አራት ብቻ ናቸው። የኛ'ኮ 20 ምናምን ሲኒማ ቤት አለን። ይህ እንዲኖር ያደረገው የተመልካቹ ቁጥር በማሻቀቡ ነው። ስለዚህ ለዚህ ተመልካች ክብርና ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ባይ ነኝ።
ሰንደቅ፡- ይህን ያህል በድክመታቸው የሚገርሙህ የፊልም ፅሁፎችን ካየህ ደፍረህ አይመጥኑኝም ብለህ የገፋሃቸው አሉ?
ሚካኤል፡- አሉ፤ ብዙ አሉ። እውነቱን ለመናገር ሳይመጥኑኝም ወይ ይሉኝታ ይዞኝ፤ ወይ ብር ቸግሮች የሰራሁት ፊልምም አለ። አሁን ያ ጊዜ አልፏል፤ ጥሩነቱ አሁን-አሁን ፊልም ማክሰርም ጀምሯል። ለምን ቢባል የተመልካችም የእይታ አቅም እያደገ ነው።
ሰንደቅ፡- አይመጥኑኝም ብለህ እንደተውካቸው ስራዎች ሁሉ ብሰራቸው ብለህ የተመኘሃቸውስ ፊልሞች አሉ?
ሚካኤል፡- አዎ አሉ! ለምሳሌ “የሎሚ ሽታ” ላይ ፊልም ብሰራ ብዬ ተመኝቻለሁ። በነገራችን ላይ ከኤልሳቤጥ መላኩ ጋር መስራት በራሱ የምናፍቀው ነገር ነው። በዚህ አጋጣሚ ከአለማየሁ ታደሰ፣ ከፍቃዱ ተ/ማርያምና ከሙሉዓለም ታደሰ ጋር መስራት እናፍቃለሁ። ሌላው፤ “ጤዛ” ፊልም እንዲሁ ብሰራበት ብዬ የተመኘሁት ፊልም ነበር።
ሰንደቅ፡- ፊልሞችን የምታየው እንደተመልካች ነው ወይስ እንደፊልም ባለሙያ?
ሚካኤል፡- ይሄን ጥያቄ እንኳን ጠየከኝ። የሚገርምህ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴአትር ተምሬ ከወጣሁ በኋላ ፊልምን በድፍረት መስራት የለብኝም በሚል ብሉናይል የፊልም ትምህርት ቤት ገብቼ ፊልም ተምሬያሁ። አንድ ዓመት ምሳ እየቋጠርኩ፤ የንግድ ፍቃዴን ሁሉ መልሼ በትክክል ነው የተማርኩት። ከዚያ ተመርቄ የወጣሁ ሰሞን እንደ አዲስ ሃያሲ ነገር አድርጎኝ ነበር። ፊልም ሳይ የመብራት አጠቃቀሙን፣ አክቲንጉን፣ ቦታ መረጣውን፣ ኤዲቲንጉን ሁሉንም ነገር አላልፍም ነበር። በኋላ ሳስበው እኔም ከፊልም ላገኝ የሚገባውን ደስታ እያጣሁ እንደሆነ ተሰማኝና ቴክኒካል ነገሩን ትቼ ወደታሪኩ ፊቴን አዞርኩ። እኔ እንደአያቴ ከማያት የእናቴ አክስት ጋር ነው ታሪክ ሲነገረኝ ያደኩት፤ በዚህ ላይ ጎረቤታችን ማይጨው የዘመቱ ሽማግሌም ነበሩ። ብዙ ታሪክ ስሰማ ነው ያደኩት። ቴአትርም ሆነ ፊልምን የተማርኩት ታሪክ ለማውራት ነው።
ቴክኒካዊ ነገሮች አያስፈልጉም ለማለት አይደለም። ነገር ግን እነሱ የመጡት ታሪኩን ለማጉላት እንደሆነ አምናለሁ። ስለዚህ አሁን አሁን ታሪኩ ላይ ብቻ አተኩሬ ነው፤ ፊልም የምመለከተው ማለት ነው። አንድን ፊልም ከወደድኩት ሁለቴ አየዋለሁ። ያኔ ነው ቴክኒካል የሆኑ ነገሮችን የማይበት።
ሰንደቅ፡- እስካሁን ከሰራሃቸው የተለየ ነው የምትውና የማትረሳው ገፀ ባህሪይ የቱ ነው?
ሚካኤል፡- በጣም የሚገርመኝ ገፀ-ባህሪይ “ሚስድኮል” የሚል ፊልም ላይ ያለው ነው። ለምን መሰለህ? የሚነሳው ከትንሽ ነገር ነው። ሰውዬው ቅናተኛ ነው። ከትንሽ ቅናት ተነስቶ የትናየት ሲደርስበት ስላሳየኝ አልረሳውም። ሌላው የምወደው “ሔሮሺማ” ላይ የነበረውን ገፀ-ባህሪይ ነው። ምናልባትም “ሔሮሺማ” ላይ ከነበሩት ገፀ -ባህሪያት በሙሉ በድጋሚ መርጠህ ውሰድ ብሏል እኔ የሰራሁትን ብቻ ነው የምመርጠው። ምን መሰለህ የቀድሞው ጦር አባል ነው፤ እሱን ገፀ-ባህሪይ ሳስበው ምን ይታየኛል፤ እኛ ሀገር በጣም ብዙ ለአገሪቱ የሚከፍሉት መሰዋዕትነት ከአገሪቱ ምንም ያልተጠቀሙ ሰዎች ናቸው። ታስታውስ ከሆነ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ በድጋሚ ጦሩን የተቀላቁሉት የቀድሞ ጦር አባላት ብዙ ናቸው፤ ለአገራቸው ሲሉ ማለት ነው። ለአገሪቱ ደራሾች ከአገሪቱ ሀብት ምንም ያልተጠቀሙ ሰዎች መሆናቸውን ሳስብ ያ ገፀ- ባህሪይ በጣም ይመስጠኛል።
ሰንደቅ፡- “ሔሮሺማ” ፊልም እንቅስቃሴ የሚጠይቅና ድካም የበዛበት ስራህ ነው የተለየ ምታስታውሰው ገጠመኝ አለህ?
ሚካኤል፡- ሰራዊት መጀመሪያ ሲፅፈው “ሔሮሺማ” ላይ የኔ ገፀ-ባህሪይ መጨረሻ ይሞት ነበር፤ እና አንድ ቀን ሰራዊት ፅፎ አደረና “በቃ አይሞትም ቆስሎ ይድናል” አለኝ። በዚህ ተጣላን። እኔ ደግሞ እንድሞት ፈልጌያለሁ ለምን መሰለህ፤ በቃ ሰውዬው ሰዎችን ለማዳን አደጋን የሚጋፈጥ ሰው ነው። እንደዚህ አይነት ሰው ዋጋውን የሚከፍለው በሞት ነው ብዬ አስብ ነበር። ስለዚህ ጉዳይ ሊያወራኝ ሰራዊት ስልክ ሲደውልልኝ እኔ ካፌ ውስጥ ነበርኩኝ። እና ጮክ ብዬ “አይደለም እኔ መሞት አለብኝ፤ እኔ'ኮ ሟች ነኝ” ስል ሁሉም ሰው ዞር ብሎ ያየኝ ነበር። አቤት ያኔ የተሰማኝ ድንጋጤ። ለማንኛውም ይህ ነገር አይረዳኝም።
ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ አንተ ካሁን በኋላ ብሰራው ብለህ ስለምትመኘው አይነት ገፀ-ባህሪይ ንገረኝ?
ሚካኤል፡- የመጀመሪያው ፊልም “ሚዜዎቹ” ስለሆነና ኮሜዲ ገፀ-ባህሪይ ስለተላበስኩ ተመልካቹም ሆነ ብዙ ዳይሬክተሮች ያን የመሰለ ገፀ-ባህሪይ እንድደጋግም ይፈልጋሉ። መረር ያሉ ገፀ-ባህሪያትን መስራት እፈልጋለሁ፤ እችላለሁም። እኔ'ኮ “ኦቴሎ” ራሱን ሆኜ ተውኛለሁ። ስለዚህ እንዲህ ከተለመድኩበት ወጣ ያሉ ነገር ግን ብዙም ሜካፕ የማይለውጣቸውን ዓይነት የውስጥ ገፀ-ባህሪያት ብሰራ ደስ ይለኛል።
ሰንደቅ፡- ስለ“ዳና” የቲቪ ድራማ ከተመልካቹ ምን ምላሽ ይደርስሃል?
ሚካኤል፡- “ዳና” ያለው የተመልካች ብዛት በጣም ያስደነግጥሃል። እርግጥ ነው ኢቲቪ በመላው አለም ከመታየቱ የመነጨ ሊሆን ይችላል፤ አንዳድ ሰው መንገድ ላይ አድናቆቱንም አስተያየቱንም ይሰጥሃል። ብዙ ሰዎችም ይደውሉልኛል፤ ያ በጣም ደስ የሚል ሞራል ነው።
ሰንደቅ፡- “ሚኪ” ስለተባለው ስለገፀ-ባህሪይ ምን ይሰማሃል፤ እንደተመልካች ስታየው?
ሚካኤል፡- በነገራችን ላይ እሁድ ጠብቄ ቤቴ አላየውም። ባለቤቴ ታየዋለች። የሁለት ዓመትና የሶስት ዓመት ልጆች አሉኝ፤ ለእነሱ አእምሮ ትንሽ ይከብዳል በሚል አሁን እነርሱ አያዩትም። እኔ ግን ወይሰኞ ጠዋት ወይም በኢንተርኔት አልያም ደግሞ ቢሮ ካልሆነ በስተቀር ከቤተሰብ ጋር አላየውም። ሚኪ (ገፀ-ባህሪው) ሰው መርዳት የሚወድና ቀጥተኛ ሰው ነው። እንደተመልካች ሳየው በጣም ነው የሚያሳዝነኝ።
ሰንደቅ፡- “ዳና” ሁለት ምዕራፎችን አልፎ ሶስተኛው ጀምሯል የማትረሳው ምን ዓይነት አጋጣሚ ነበረህ?
ሚካኤል፡- “ዳና” ላይ በጣም የሚገርመኝ የኔ ገፀ-ባህሪ አለ (ሚኪ) ተፃራሪው ደግሞ ጓደኛው ቢኒያም (ሚኪያስ መሀመድ) አለ። ያው በድራማው ውስጥ ያለችውን ፍቅረኛዬን ሊነጥቀኝ የሚያሴር ገፀ-ባህሪይ ነው። የሚገርመው ሚኪያስ መሀመድ በተፈጥሮው ሽቅርቅር ነው። አለባበሱ ጥንቅቅ ብሎ የሚመጣ አይነት ሰው ነው። እኔ ደግሞ እሱ ነገር አይሳካልኝም። እናም በቀረፃ ወቅት ስንሰባሰብ ምን ይባላል መሰለህ?” ግን እስቲ ምን ታደርግ (ፍቅረኛዬን ነው) ቢኒ እንዴት እንደሚያምር ተመልከቱት ይሄኛው (እኔን ነው) ደግሞ አፈር መስሎ ነው የመጣው “ይላሉ (ሳቅ). . . ይሄ አስተያየት ብዙ ጊዜ ይሰማል። እስቲ ዘንጠህ ና እባልና አለኝ የምለውን ለባብሼ እመጣለሁ ግን ሁልጊዜ አይሳካልኝም። አንዳንድ ሰዎችም “ፍቅረኛህ ወደሱ ብትሄድም አይፈርድባትም እኮ” ይሉኛል። “ዳና” ከብዙ ሰዎች ጋር ያስተዋወቀኝ ስራ ነው።
ሰንደቅ፡- የራስህን አዲስ ፊልም እየሰራህ ስለመሆኑ ነግረኸኛል እስቲ ስለሱም ትንሽ እናውራ?
ሚካኤል፡- አዎ የበኩር ስራዬ ነው “ጥቁር እንግዳ” ይሰኛል ርዕሱ፤ ይህ ፊልም መስራት እችላለሁ ብዬ በራሴ እስክተማመን አቆይቼ የሰራሁት ስራ ነው። ፅሁፉን ለብዙ ባለሙያዎች አሳይቻለሁ። ጥሩ-ጥሩ ሃሳቦችን አግኝቻለሁ። በትወናው ላይም አድማሱ ከበደ፣ ድርበወርቅ ሰይፉ፣ መኮንን ላዕከና ዝናህብዙ ፀጋዬ አሉበት። ትልቁ ፈተና ግን አዳዲስ ልጆችም ያሉበት መሆኑ ነው። ልጆቹ ጀማሪዎች ይሁኑ እንጂ ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው እስከዳር ግርማይ እና ሮቤል ሰይድ የሚባሉ ልጆችን አካትቼበታለሁ። እኔም ከፅሁፉና ከዳይሬክተርነቱ በተጨማሪ በትወናው ተሳትፌያለሁ። “ጥቁር እንግዳ” አሁን ተጠናቋል። ሐምሌ ውስጥ ተመርቆ ለዕይታ ይበቃል የሚል ተስፋ አለኝ።
ሰንደቅ፡- የመጨረሻው ጥያቄዬ ሚኪ በምን ይዝናናል?
ሚካኤል፡- በጣም የሚያዝናናኝ ኳስ ነው። ውጤት አልባ ሆኑ እንጂ ከሀገር ውስጥ የቡና፤ ከውጪ ደግሞ የአርሰናል ደጋፊ ነኝ። ከኳስ ሌላ እንደመዝናኛ ከታየ የታሪክ መፅሀፍትን አነባለሁ፤ ፊልም አያለሁ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከልጆቼ ጋር በማሳለፈው ጊዜ በጣም ደስተኛ ነኝ። ልጆቼ ኖህ ሚካኤል እና ኖአሚን ሚካኤል ይባላሉ። በጣም እወዳቸዋለሁ።
Source: Sendek Newspaper